የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን አገልግሎቱ በሁለት የሰው ኃይል ማለትም በአንድ የኦዲት አገልግሎት ኃላፊ እና በአንድ ኦዲተር የተደራጀ ነው፡፡ 

የኦዲት አገልግሎቱ የኮሚሽኑን  የፋይናንስ መረጃዎችንና መግለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመርና የመምሪያዎችን፣ የአገልግሎቶችንና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን የሥራ ክንውን በመገምገም የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ሆኖ የኦዲት ሪፖርቱንም የሚያቀርበው በቀጥታ ለኮሚሽነሩ ነው፡፡  

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት መካከል፡-

የፋይናንስ መረጃዎችንና መገለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመር መረጃዎቹ የኮሚሽኑን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ማሳየት አለማሳየታቸውን በማየት የኦዲት አስተያየት ማቅረብ፣
መምሪያዎችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ያቀዱትን ሥራ ማከናወናቸውን መገምገም፣
በቂና አስተማማኝ የፋይናንስ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን በመገምገም የማሻሻያ ሃሳቦችን ማቅረብ፣
መምሪያዎች፣ አገልግሎቶችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ኮሚሽኑ ያለውን ሃብትና ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ የክዋኔ ኦዲት ማካሄድ፣
መሻሻል በሚገባቸው የኮሚሽኑ የገንዘብ አስተዳደር አሰራሮች ላይ የማሻሻያ አስተያየት የማቅረብ፣
ጥሬ ገንዘብና ሰነዶች በተለይም ቼኮች፣ የቼክ ጉራጆች፣ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኞችና ማስረጃዎች በአግባቡ መጠበቃቸውን መከታተል፣ የክፍያ ሰነዶች የሂሳብ ስሌት ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣  

እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ማከናወን ለአገልግሎቱ የተሰጡ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡