የሥነምግባር ትምህርት እና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ መገናኛ ብዙኃንን፣ የኮሚሽኑን ሕትመቶች፣ የፊት ለፊት ግንኙነቶችንና ሌሎች አመቺ ዘዴዎችን በመጠቀም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሥነ ምግባር ትምህርትን በማስፋፋትና በማስረጽ እንዲሁም የኮሚሽኑን ራዕይ፣ ተልዕኮና እንቅስቃሴ በማሳወቅ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በዋነኝነት ለማከናወን የተደራጀ ነው፡፡ 

መምሪያው በዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን የሥነምግባር ትምህርት እና የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥኖችን በመያዝ የተደራጀ ነው፡፡ እነዚህም ዲቪዥኖች በምክትል ዳይሬክተር ይመራሉ፡፡ እያንዳንዱ ዲቪዥን ደግሞ በሁለት ቡድኖች ይከፋፈላል፡፡ በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርት ዲቪዥን በስሩ የመደበኛ ትምህርት ተቋማት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን እና የመንግሥት መ/ቤቶችና የሲቪል ማህበራት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን ያካትታል፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ደግሞ በበኩሉ የመገናኛ ብዙኃን ዝግጅት ቡድንን እና የሕዝብ ግንኙነት ቡድንን ያቅፋል፡፡  

በዚህ መሠረት የመምሪያው የሥራ እንቅስቃሴ የሚመራው በአንድ ደይሬክተር፣ በሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች እና በአራት የቡድን ኃላፊዎች ሆኖ በአጠቃላይ በ28 የሰው ኃይል የተደራጀ ነው፡፡ 

በመምሪያው ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲኘሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ የሙያ ስብጥራቸውም ቋንቋና ሥነጽሁፍ፣ ትምህርትን፣ ፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት፣ ትያትር አርትስ፣ ሥርዓተ ትምህርት እና ከሙኒኬሽን ሳይኮሎጂን ያጠቃልላል፡፡ ባለሙያዎቹም በአብዛኛው በማስተማር፣ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት በጋዜጠኝነት፣ በአሰልጣኝነት ወዘተ የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ 

ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ እንደማይችል ሙስናን ለመከላከል የተደረጉ የሌሎች ሀገሮች ጥረቶች ተሞክሮ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በሙስና ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ከሚደረገው የምርመራ እና የክስ ሂደት ጐን ለጐን ሙስና እና ብልሹ አሠራር በአንድ አገር ላይ ስለሚያደርሱት የከፋ ጉዳት ሕብረተሰቡን በስፋት ማስተማር አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ሙስናን የመዋጋቱ ተግባር በአንድ ተቋም ብቻ እየተከናወነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ሙስናን የማይሸከም ሕብረተሰብ በመፍጠር በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ የሁሉንም ሕብረተሰብ ተሳትፎ ማግኘት የግድ ነው፡፡ 

በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከተለያዩ ተቋማትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር በመልካም ሥነምግባርና በፀረ-ሙስና ዙሪያ የተለያዩ የማስተማር ዘዴዎችን በመጠቀም ትምህርት ይሰጣል፡፡ መምሪያው ከሚከተላቸው የማስተማር ዘዴዎች መካከል፡-

መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣
የኮሚሽኑን የኘሬስ ውጤቶች በማዘጋጀት፣
በግንባር (face to face) በመገናኘት እና
ቅንጅት በመፍጠር

የሚያከናውናቸው ትምህርታዊ አቀራረቦች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 

መምሪያው ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ባለፉት አራት አመታት ቁጥራቸው 266 የሚሆኑ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በማቋቋምና እነዚህን የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች በኃላፊነት የሚመሩ የሥነምግባር መኮንኖችን በሠራተኛው እንዲመረጡ በማድረግ መልካም ሥነምግባርን ለማስፋፋትና ሙስናን ለመዋጋት የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል፣

የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች የሥራ መመሪያ ዝግጅት፣
የሥነምግባር መኮንኖች መምረጫ መስፈርት ዝግጅት፣
የሥነምግባር መኮንኖቹ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲረዳቸው የሚያስችል ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉ፣

   በዐበይነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡