የአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ

 የአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ በዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን በውስጡም የፋይናንስ ዩኒት፣ የሰው ኃይልና ስልጠና ዩኒት፣ የንብረት አስትዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒት እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዩኒትን ይይዛል፡፡ መምሪያው ከዳይሬክተር በተጨማሪ ምክትል ዳይሬክተር አለው፡፡ ምክትል ዳይሬክተሩም በዋነኛነት የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒትን በበላይነት ይመራል፡፡ መምሪያው በአራቱም ዩኒቶች ወደ ሰባ የሚጠጋ የሰው ኃይል አለው፡፡

 እያንዳንዱ ዩኒት በዋነኛነት የሚያከናውነውን ተግባር ለመዘርዘር ያህል የመምሪያው የፋይናንስ ዩኒት በተለይ ከፋይናንስ አስተዳደርና ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያደራጃል በዚህ መሠረት የኮሚሽኑን የተለያዩ መሣሪያዎችና አገልግሎቶች በጀት በማዘጋጀት የኮሚሽኑን አጠቃላይ የገንዘብ አጠቃቀምና አያያዝ ይቆጣጠራል፡፡

 የሰው ኃይልና ስልጠና ዩኒት የኮሚሽኑን ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ በመከተል ለኮሚሽኑ የሚያስፈልጉ ሠራተኞችን በቅጥር፣ በዝውውርና በእድገት እንዲሟሉ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ተገቢውን ሥልጠና እንዲያገኙ በየጊዜው ክትትል በማድረግ የሚያስፈፅም ሲሆን በተጨማሪም የሠራተኞችን የጡረታ፣ የሥራ መልቀቂያ፣ የፈቃድ እና ሌሎች ጉዳዮችን ያስፈፅማል፡፡

 የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒት ደግሞ ለኮሚሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በመግዛት ያሠራጫል፣ ያስተዳድራል፣ የጥገና ጉዳዮችንም ተከታትሎ ያስፈፅማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑን ተሽከርካሪዎች የማስተዳደር፣ የማሰማራት የማስጠገን እና የኢንሹራንስ ጉዳዮችን የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ለዚህ ዩኒት ነው፡፡ የኮሚሽኑን ሕንፃ የማስተዳደር፣ ልዩ ልዩ ጥገናዎችን የማስፈፀም፣ የአገልግሎት ክፍያዎችን የመፍቀድ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን ማከናወን የዚህ ዩኒት የሥራ ድርሻ ነው፡፡

 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዩኒትም ተጠሪነቱ ለአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለኮሚሽኑ የሚያስፈልገውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚያከናውነው ይህ የሥራ ክፍል ነው፡፡

 

 የኦዲት አገልግሎት

የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን አገልግሎቱ በሁለት የሰው ኃይል ማለትም በአንድ የኦዲት አገልግሎት ኃላፊ እና በአንድ ኦዲተር የተደራጀ ነው፡፡ 

የኦዲት አገልግሎቱ የኮሚሽኑን  የፋይናንስ መረጃዎችንና መግለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመርና የመምሪያዎችን፣ የአገልግሎቶችንና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን የሥራ ክንውን በመገምገም የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ሆኖ የኦዲት ሪፖርቱንም የሚያቀርበው በቀጥታ ለኮሚሽነሩ ነው፡፡  

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት መካከል፡-

የፋይናንስ መረጃዎችንና መገለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመር መረጃዎቹ የኮሚሽኑን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ማሳየት አለማሳየታቸውን በማየት የኦዲት አስተያየት ማቅረብ፣
መምሪያዎችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ያቀዱትን ሥራ ማከናወናቸውን መገምገም፣
በቂና አስተማማኝ የፋይናንስ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን በመገምገም የማሻሻያ ሃሳቦችን ማቅረብ፣
መምሪያዎች፣ አገልግሎቶችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ኮሚሽኑ ያለውን ሃብትና ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ የክዋኔ ኦዲት ማካሄድ፣
መሻሻል በሚገባቸው የኮሚሽኑ የገንዘብ አስተዳደር አሰራሮች ላይ የማሻሻያ አስተያየት የማቅረብ፣
ጥሬ ገንዘብና ሰነዶች በተለይም ቼኮች፣ የቼክ ጉራጆች፣ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኞችና ማስረጃዎች በአግባቡ መጠበቃቸውን መከታተል፣ የክፍያ ሰነዶች የሂሳብ ስሌት ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣  

እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ማከናወን ለአገልግሎቱ የተሰጡ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

 የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ  

መምሪያው በመንግሥት መ/ቤቶች ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም የፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች ከሚሰጠው ድጐማ ጋር በተያያዘ በክልል መ/ቤቶች በወንጀል ሕግ እና በሌሎች ሕጐች ውስጥ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች በመንግሥት ሠራተኞች ወይም ባለሥልጣኖች ወይም በሌሎች ሰዎች ስለመፈፀማቸው ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው የመመርመር  ወይም እንዲመረመር የማድረግ ተግባርና ኃላፊነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር የመምሪያው ዋና ተግባር የተጠረጠሩ የሙስና ወንጀሎችን እና የሥነምግባር ጥሰቶችን በማጣራት ጥፋተኞች ክስ እንዲመሰረትባቸው የምርመራውን ውጤት ለዐቃቤ ሕግ መምሪያ ማስተላለፍ ነው፡፡ 

በመሆኑም መምሪያው ከተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች የሚደርሱትንና በሙስና ወንጀል እና በሥነምግባር መተላለፍ ዙሪያ የሚያተኩሩ ጥቆማዎችን በአካል፣ በስልክ ወይም በደብዳቤ በፋክስ እና በኢሜል አማካኝነት በመቀበል እንደችግሩ ይዘትና ስፋት ጥቆማው በቅደም ተከተል የሚደራጅበትንና ለምርመራ ዝግጁ የሚሆንበትን አሠራር ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ መምሪያው የተጠርጣሪዎች ሀብት በፍርድ ቤት አማካኝነት እንዳይንቀሳቀስ በማስወሰን ተጠራጣሪዎቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ ፍርድ ቤት በሚወስነው መሠረት የታገደው ንብረት ለፍርድ ማስፈፀሚያ እንዲውል ሊያደርግ ይችላል፡፡ 

ከሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ ባለሙያዎች መካከል አንድን የተጠረጠረ የሙስና ወንጀል ጉዳይ እንዲመረምር የተመደበ ሠራተኛ ለምርመራ ሂደቱ ጠቃሚነት አለው ተብሎ እስከታመነበት ድረስ ከማንኛውም ድርጅት ወይም ግለሰብ መረጃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ምርመራቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪ የሙስና ወንጀሎችን ጉዳይ በተመለከተ መረጃ እንዲሰጥ የሚጠየቅ ማንኛውም አካል በተጠየቀው ጉዳይ ላይ መረጃ ለመስጠት ትብብር ሊያሳይ የሚገባው መሆኑን ነው፡፡ 

የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ ዳይሬክተር በሙስና የተጠረጠረን ግለሰብ ወይም ጉዳይ በምርመራ ላይ የሚገኝን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንዲውል የሚያስገድድ አሳማኝ ምክንያት ካለው ከ48 ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ በቁጥጥር ስር እንዲውል ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን አለው፡፡ ይህም ሲሆን ጉዳዩን በቅድሚያ ለሥነ ምግባርና ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሳውቆ ስምምነት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ 

በሌላ ወገን ደግሞ ማንኛውም የመንግሥት ተቋምም ሆነ ግለሰብ ከባድ የሥነምግባር መጣስን ጨምሮ  የሙስና ወንጀል ለመፈፀሙ ጥርጣሬ ሲኖረው ጉዳዩን ለኮሚሽኑ እንዲጠቁም ይጠበቃል፡፡ 

የተወሰኑ የመምሪያው ተግባራት እንዳስፈላጊነቱ በሚስጥር የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ መንግሥታዊ ተቋም የሙስና ወንጀል ለመፈፀሙ ጥቆማ ለማቅረብ ወደ ኮሚሽኑ የሚመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማንነት በሚስጥር ሊጠበቅላቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም በጅምር የምርመራ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጉዳይ በወንጀሉ ተጠያቂ አካላት እንዳይጠፉና ተፈላጊ መረጃዎቹም እንዳይሰወሩ ለማድረግ በሚስጥር ተጠብቆ መቆየቱ ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን የሙስና ወንጀልን የማጣራት ሂደት በሚስጢር ተጠብቆ የሚቆየው ተጠርጣው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ብቻ ነው፡፡ 

መምሪያው በጥቆማ የሚቀርቡለትን የተጠረጠሩ የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ አንዱን ከሌላው ሳያበላልጥ ለሁሉም እኩል ትኩረት ሰጥቶ ምርመራ ሥራውን ያካሂዳል ምክንያቱም በጥቆማ አቀራረብ ላይ ዝቅተኛ የሙስና ወንጀል ጉዳይ መስለው የሚታዩ ጉዳዮች በምርመራ ሂደት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ያካተቱ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ ወገን ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በፀረ-ሙስና ዘመቻው ላይ የሚያሳየው ተሳትፎ የተጠናከረ እንዲሆን ከተፈለገ ሁሉም ዜጋ ለኮሚሽኑ በጥቆማ የሚያቀርባቸው የሙስና ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው መጣራት ስለሚገባቸው ነው፡፡

ይህም በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሙስና ወንጀሎች ሳይቀሩ በኮሚሽኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉ ሙስናን ሊሸከም የማይችል  ሕብረተሰብ  ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የትኛውም የሙስና ወንጀል ከሕዝብ ዕይታ ተሰውሮ ብዙ እንዳይቆይ ያደርጋል፡፡

 የሙስና መከላከልና ምርምር መምሪያ

 የሙስና መከላከልና ምርምር መምሪያ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሙስና ወንጀልና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ከኮሚሽኑ ዓላማ አስፈፃሚ መምሪያዎች አንዱ ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ 

መምሪያው የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ይችል ዘንድ 28 ባለሙያዎችንና የሥራ ኃላፊዎችን በመያዝ በሦስት ዲቪዥኖች ተደራጅቶ ይገኛል፡፡ ዲቪዥኖቹም፡-

የሙስና መከላከልና ምርምር ዲቪዥን አንድ
የሙስና መከላከልና ምርምር ዲቪዥን ሁለት
የሥነምግባር ምርምር ማዕከል ዲቪዥን ሦስት ሲሆኑ፣ በሰው ኃይል በኩል ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንድ የመምሪያ ዳይሬክተር፣ ሦስት ምክትል ዳይሬክተሮችና ሁለት ፀሐፊዎች ይገኙባቸዋል፡፡

መምሪያው በአዋጅ ቁጥር 433/97 ኮሚሽኑ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከመከላከል ጋር የተያያዙት  ሥልጣንና ተግባራት በቀጥታ ይመለከቱታል፡፡ እነዚህም ሥልጣንና ተግባራት ጠቅለል ብለው ሲታዩ፡-

የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችን ማካሄድ፣  
የምርመራ ሥራና የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት ስር ሊጠቃለሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

መምሪያው  እስካሁን ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት

መምሪያው ከላይ የተገለፀውን አደረጃጀትና የሰው ኃይል በመያዝ የሚከተሉትን ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 

የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችና የምርምር ሥራ

የሙስና መከላከልና ምርምር መምሪያ የመንግሥት መ/ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማዕከል በማድረግ የአሠራር ሥርዓት ጥናቶች ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንፃር እስከአሁን ድረስ በመምሪያው 19 የሚደርሱ መንግሥታዊ ተቋማት የአሠራር ሥርዓቶች ተጠንተው የተጠናቀቁ ሲሆን 5 መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ በመጠናት ላይ  ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን መምሪያው ከሙስና እና ከሥነምግባር ጋር የተያያዙ የምርምር ጥናቶችንም ያካሂዳል፡፡

የምርምር ሥራ፣ የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ ዝግጅት

ከሙስና እና ከሥነምግባር ጋር የተያያዙ የምርምር ጥናቶችን ማካሄድና የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ ሕግ ለማስፈፀም የሚያግዙ ደንቦችና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ለሚመለከታቸወ አካላት አስቀርቦ እንዲፀድቅ ክትትል የማድረግ ሥራዎችን ማከናወን ከመምሪያው የሚጠበቅ ሁለተኛው ዐቢይ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ 

መምሪያው የአሠራር ሥርዓት ጥናት እና የምርምር ስራዎችን ለመፈፀም የሚከተላቸው ስልቶች 

በመንግሥት መ/ቤቶች እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡና መጋለጥ የሚችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን በማጥናት እንዲሻሻሉ የማማከርና የማሳሰብ አገልግሎቶችን ቁጥራቸው ከ36ዐ ለሚበልጡ የመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች በአንድ ጊዜ ለማከናወን ኮሚሽኑ አሁን ባለው ውስን የሰው ኃይልና አደረጃጀት አዳጋች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የግዴታ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚጠኑ ተቋማትን መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡ 

በመሆኑም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት ተቋማትን የአሠራር ሥርዓት ጥናት ለማካሄድ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚጠኑ መንግሥታዊ ተቋማትን ለመምረጥ የሚያስችሉ መስፈርቶች የያዘ የመምረጫ መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል፡፡ 

ከሕዳር 1997 ዓ.. ጀምሮ ደግሞ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር ከተጋለጡ የመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች መካከል ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የአሠራር ሥርዓት ጥናት የሚካሄድባቸውን ተቋማት ለመለየትና ደረጃ ለማውጣት የሚያስችል መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ 

መምሪያው የአሠራር ሥርዓቶቻቸው የሚጠኑ ተቋማትን ለመምረጥ ከሚጠቀምበት መመሪያ በተጨማሪ የተመረጡት ተቋማት የአሠራር ሥርዓት ምን ላይ ተጀምሮ የት መጠናቀቅ እንዳለበት የሚያመላክት የአሠራር ሥርዓት የአፈፃፀም መመሪያ አዘጋጅቶ ተፈፃሚ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

መምሪያው ይህን የአሠራር ሥርዓት ጥናት መመሪያ ተከትሎ ሥራን ለማቀላጠፍና የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማትን የአፈፃፀም ብቃትና የአሠራር ሥርዓቶች በተፋጠነ ሁኔታ ለማጥናት የሚያስችለው አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ አዲስ መመሪያ አምስት ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ 

እነዚህም፡-

1.      በመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ያሉና የተቋቋሙ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች የየመ/ቤቶቻቸው ሥራዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ እንዳይሆኑ የአሠራር ሥርዓት ጥናት እንዲያካሂዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና በጥናት ሂደቱ ላይ በየደረጃው የሚፈለገውን ድጋፍ መስጠትና መከታተል፣

2.      ከልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ስትራቴጂ አንፃር ቁልፍ ሚና የሚጫወቱና ለሙስናና ለብልሹ አሠራር በመጋለጣቸው በአጠቃላይ በተያዘው የልማትና የዲሞክራሲ ጐዳና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ በሚችሉ ተቋማት ላይ ከሌሎች ተቋማት የበለጠ ትኩረት በመስጠትና የመምሪያውን ባልደረቦች በእነዚህ ተቋማት በቋሚነት ወይም በተወሰነ ጊዜ በዙር መድቦ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ አሠራሮች እንዲሻሻሉ በየጊዜው መፈተሽና ተግባራዊነቱን በቋሚነት መከታተል፡፡

3.      በመምሪያው በተዘጋጀው የአሠራር ሥርዓቶቻቸውን ለማጥናት መምረጫ መመሪያ መሠረት የተቋማቱን ሥራዎችና የአሠራር ስርዓቶች መፈተሽ፣ ማጥናት፣ የመፍትሄ ሃሳብ መጠቆም፣

4.      በተለያየ መልኩ/ ከጥቆማ፣ ከሚዲያ፣ ከምርመራ መምሪያ ከበላይ አካል ወዘተ/ ለመምሪያው ከሚቀርቡ (specific) ጉዳዮች መካከል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት የአሠራር ሥርዓት ጥናት ማድረግና እንዲሻሻሉ የሚያስችል ምክር መስጠት፣

5.      የአንድ መ/ቤትን አሠራር እንዲሻሻል ግቡ ያደረገ ሳይሆን አጠቃላይ ጥናት የሚያስፈልጋቸውን ሥራዎች/ ለምሳሌ የግዥ አፈፃፀም፣ የንብረት አስተዳደር፣ የፋይናንስ አስተዳደር ወዘተ...) ከሙስና አንፃር ያላቸውን ተጋላጭነት በመለየትና በማጥናት ተቀባይነት ያለው መመሪያ ማዘጋጀትና ለተጠቃሚ ክፍሎች አሠራራቸውን እንዲፈትሹት ማሰራጨት፣ ውጤቱን በሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች አማካኝነት መከታተል ናቸው፡፡ 

የተሻሻለው ይህ የአሠራር ሥርዓት ጥናት መመሪያ ከላይ ከተገለፁትና የመመሪያው አካል ከሆኑት ጉዳዮች በተጨማሪ የድህረ አሠራር ሥርዓት ጥናት አፈፃፀም ክትትል ሥራ የት ተጀምሮ እንዴት ተከናውኖ በምን ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚያመላክት አሠራርን ዝርዝር ይዞ ይገኛል፡፡

ዐቃቤ ሕግ መምሪያ

 የፀረ-ሙስና ዐቃቤ ሕግ መምሪያ በፌደራሉ የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥር ከተደራጁት ዓላማ አስፈፃሚ መምሪያዎች አንዱ ነው፡፡ መምሪያው የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው በቂ ባለሙያዎች እንዲኖሩት ሆኖ የተቋቋመ ነው፡፡  

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የተወሰኑ ዐቃቢያነ ሕጐች ብቻ ያሉት በመሆኑ የሰው ኃይል እጥረት የሚታይበት ነው፡፡ 

መምሪያው የተደራጀበት ዋና ዓላማ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ የተጣራባቸውን ፋይሎች መርምሮ ወንጀል ፈፃሚ ተጠርጣሪዎችን ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ክስ መስርቶ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እና በሙስና ወንጀል የተገኘን ንብረት በማሳገድ እና እንዲወርስ በማድረግ በፀረ-ሙስና ትግሉ ጉልህ የሙስና ወንጀል የመከላከል ተግባርን ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡ 

ይህን ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ መምሪያው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-

·        በወንጀል ሕግ እና በሌሎች ሕጐች የሙስና ወንጀሎች ፈፅመዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ የተጣራባቸው የምርመራ መዛግብት ሲደርሱት በማጥናትና በመመርመር በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸውን ክስ ሊቀርብባቸው አይገባም የሚል ውሣኔ በመስጠት ይዘጋል፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን የምርመራ መዝገቦች ተጨማሪ ምርመራ ተደርጐ ምርመራው ተጠናክሮ ውጤቱ እንዲቀርብለት ለመርማሪው አካል ይመልሳል፣ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ በተሰባሰበባቸው የሙስና ወንጀል ምርመራ መዝገቦች ላይ የወንጀል ክስ በፍ/ቤት መስርቶ ተገቢውን በመፈፀም የመፋረድ፣

·        በሙስና ወንጀል ድርጊት ከተገኘ ንብረት ጋር በተያያዘ በምርመራ ላይ ያሉ ሰዎች ሀብት በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ የማሳገድ፣

·        በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ የተረጋገጠን ማንኛውንም ንብረት ወይም ሀብት በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲወረስና በሀራጅ ተሸጦ ወይም ሳይሸጥ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን የማድረግና

·        ስለመመርመርና ስለመክሰስ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነሥርዓትና በሌሎች ሕጐች ለዐቃቤ ሕግ በተሰጠ ሥልጣን መሠረት ኮሚሽኑን በሚመለከቱ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ላይ ተገቢውን የመፈፀም ተግባራትን ያከናውናል፡፡ 

የፀረ-ሙስና  ዐቃቤ  ሕግ መምሪያ ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት

ከኮሚሽኑ ምርመራ መምሪያ እና ከሌሎች የምርመራ አካላት ጋር

መምሪያው ግንኙነቱ በግንባር ቀደምትነት የተመሠረተው በኮሚሽኑ ሥር ከተደራጀው የምርመራ መምሪያ ጋር ሲሆን ይህ መምሪያ ከዐቃቤ ሕግ መምሪያ ጋር ያለው ግንኙነት የተመሠረተው ራሱ ባሉት መርማሪዎች አማካኝነት በሚያከናውናቸው የምርመራ ተግባራት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ማለትም በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መምሪያ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ መምሪያዎች እና በክልል መንግሥታት ፖሊስ የምርመራ መምሪያ ምርመራቸው የተጠናቀቁ መዛግብት ለዐቃቤ ሕግ መምሪያ የሚደርሱት በኮሚሽኑ ምርመራ መምሪያ በኩል በመሆኑ ሁለቱ የኮሚሽኑ መምሪያዎች የጠበቀ የዕለት ተዕለት የሥራ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎችን በመያዝ፣ ለምስክሮች መጥሪያ በማድረስ እንዲሁም የሚታገዱ ንብረቶችን በማጥናት በኩል የሚደረገው የሥራ ግንኙነት ሁለቱን በጋራ የሚያገናኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡ 

ከፍርድ ቤቶች ጋር  
የፀረ-ሙስና አቃቤ ሕግ መምሪያ ከምርመራ መምሪያ ቀጥሎ ከፌደራል ፍርድ ቤቶች እና ከክልል  ጠቅላይ  ፍርድ ቤቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው፡፡ የግንኙነቱም መሠረት መምሪያው በፍርድ ቤቶች የሚያስከፍታቸው የሙስና ወንጀል ክስ ፋይሎች ሲሆኑ ትክክለኛ ፍትህ ሳይዘገይ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻች በጋራ ይሰራሉ፡፡ 
ከሌሎች የዐቃቤ ሕግ ተቋማት ጋር

የፀረ-ሙስና ዐቃቤ ሕግ መምሪያ በፌደራራሉ የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥር ከተደራራጀበት ከ1993 ዓ.. ጀምሮ ከሌሎች የዐቃቤ ሕግ ተቋማት ጋር የተመሠረተ ቀጥተኛ የሆነ የሥራራ ግንኙነት ባይኖርም አልፎ አልፎ ከኮሚሽኑ ሥልጣን ክልል ውጭ የሆኑ የምርመራራ መዛግብት ሲያጋጥሙ በመሸኛ መረጃ የሚለዋወጡበት አሠራራር የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ወደፊት የተሻሻለውን የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 መሠረት በማድረግ የፌዴራራሉም ሆነ የክልል ዐቃቤ ሕግ ተቋማት እና የክልል ሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤያነ-ሕግ የፌዴራራሉን መንግሥት እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግን ወክለው የፌዴራራሉን መንግሥት የሚመለከቱ የሙስና ወንጀሎችን ሲከሱና ሲከራራከሩ በብዙ መንገድ ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚኖር ይታመናል፡፡

 የሥነምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

 የሥነምግባር ትምህርት እና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ መገናኛ ብዙኃንን፣ የኮሚሽኑን ሕትመቶች፣ የፊት ለፊት ግንኙነቶችንና ሌሎች አመቺ ዘዴዎችን በመጠቀም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሥነ ምግባር ትምህርትን በማስፋፋትና በማስረጽ እንዲሁም የኮሚሽኑን ራዕይ፣ ተልዕኮና እንቅስቃሴ በማሳወቅ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በዋነኝነት ለማከናወን የተደራጀ ነው፡፡ 

መምሪያው በዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን የሥነምግባር ትምህርት እና የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥኖችን በመያዝ የተደራጀ ነው፡፡ እነዚህም ዲቪዥኖች በምክትል ዳይሬክተር ይመራሉ፡፡ እያንዳንዱ ዲቪዥን ደግሞ በሁለት ቡድኖች ይከፋፈላል፡፡ በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርት ዲቪዥን በስሩ የመደበኛ ትምህርት ተቋማት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን እና የመንግሥት መ/ቤቶችና የሲቪል ማህበራት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን ያካትታል፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ደግሞ በበኩሉ የመገናኛ ብዙኃን ዝግጅት ቡድንን እና የሕዝብ ግንኙነት ቡድንን ያቅፋል፡፡  

በዚህ መሠረት የመምሪያው የሥራ እንቅስቃሴ የሚመራው በአንድ ደይሬክተር፣ በሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች እና በአራት የቡድን ኃላፊዎች ሆኖ በአጠቃላይ በ28 የሰው ኃይል የተደራጀ ነው፡፡ 

በመምሪያው ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲኘሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ የሙያ ስብጥራቸውም ቋንቋና ሥነጽሁፍ፣ ትምህርትን፣ ፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት፣ ትያትር አርትስ፣ ሥርዓተ ትምህርት እና ከሙኒኬሽን ሳይኮሎጂን ያጠቃልላል፡፡ ባለሙያዎቹም በአብዛኛው በማስተማር፣ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት በጋዜጠኝነት፣ በአሰልጣኝነት ወዘተ የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ 

ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ እንደማይችል ሙስናን ለመከላከል የተደረጉ የሌሎች ሀገሮች ጥረቶች ተሞክሮ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በሙስና ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ከሚደረገው የምርመራ እና የክስ ሂደት ጐን ለጐን ሙስና እና ብልሹ አሠራር በአንድ አገር ላይ ስለሚያደርሱት የከፋ ጉዳት ሕብረተሰቡን በስፋት ማስተማር አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ሙስናን የመዋጋቱ ተግባር በአንድ ተቋም ብቻ እየተከናወነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ሙስናን የማይሸከም ሕብረተሰብ በመፍጠር በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ የሁሉንም ሕብረተሰብ ተሳትፎ ማግኘት የግድ ነው፡፡ 

በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከተለያዩ ተቋማትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር በመልካም ሥነምግባርና በፀረ-ሙስና ዙሪያ የተለያዩ የማስተማር ዘዴዎችን በመጠቀም ትምህርት ይሰጣል፡፡ መምሪያው ከሚከተላቸው የማስተማር ዘዴዎች መካከል፡-

መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣
የኮሚሽኑን የኘሬስ ውጤቶች በማዘጋጀት፣
በግንባር (face to face) በመገናኘት እና
ቅንጅት በመፍጠር

የሚያከናውናቸው ትምህርታዊ አቀራረቦች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 

መምሪያው ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ባለፉት አራት አመታት ቁጥራቸው 266 የሚሆኑ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎችን በማቋቋምና እነዚህን የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች በኃላፊነት የሚመሩ የሥነምግባር መኮንኖችን በሠራተኛው እንዲመረጡ በማድረግ መልካም ሥነምግባርን ለማስፋፋትና ሙስናን ለመዋጋት የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል፣

የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች የሥራ መመሪያ ዝግጅት፣
የሥነምግባር መኮንኖች መምረጫ መስፈርት ዝግጅት፣
የሥነምግባር መኮንኖቹ ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲረዳቸው የሚያስችል ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉ፣

   በዐበይነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

 

የሕግ አገልግሎት  

የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሕግ አገልግሎት ተጠሪነቱ ለኮሚሽነሩ ሲሆን የአገልግሎት ኃላፊና አንድ የሕግ አማካሪ   ይዞ የተደራጀ ነው፡፡     

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል

·        ከኮሚሽኑ በሚቀርቡለት ጉዳዮች ላይ የህግ ምክር መስጠት፣

·        የህግ ሰነዶችን ማዘጋጀት እንዲሁም በሌሎች መምሪያዎችና አገልግሎቶች በሚዘጋጁ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ አስተያየት መስጠት፣ በሥራ ላይ ያሉ ደንቦችንና መመሪያዎችን  ችግር እያጠና  የማሻሻያ  ሀሳቦችን ማቅረብ፣

·        ኮሚሽኑን በሕግ ክርክር/ ጉዳይ/ መወከል፣

·        በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በመመስረት ደንብና መመሪያዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም በሌሎች ተዘጋጅቶ ሲቀርብ በማዳበር ማጠናቀቅ፣

·        የቅጥርና የግዥ ውል ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡ 

ባለፉት ሦስት ዓመታት አገልግሎቱ የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን በተለይም በኮሚሽኑ ተፈፃሚ ሲሆን በቆየው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ኘሮግራም ላይ በመሳተፍና የኮሚሽኑ የተለያዩ መምሪያዎችና አገልግሎቶች ማሻሻያ ኘሮግራሙን ተፈፃሚ እንዲያደርጉ በመርዳት እገዛ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የ2ዐ መመሪያዎች ዝግጅት የተከናወነ ሲሆን ከቅሬታ ጋር በተያያዘና በሌሎችም ምክንያቶች ለቀረቡ ከ15ዐ በላይ በሆኑ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ የሕግ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎቱ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች 1ዐዐ የሚሆኑ ረቂቅ የኮንትራት ስምምነቶችን በማዘጋጀት ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር  የሕግ ውል እንዲገባ ድጋፍ አድርጓል፡፡ 

የኘላንና ኘሮግራም አገልግሎት  

አገልግሎቱ ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን በውስጡም ከአገልግሎቱ ኃላፊ በተጨማሪ የአንድ ኤክስፐርት፣ የአንድ ስታትስቲሽያን እና የአንድ ፀሐፊ የሥራ መደቦችን እንዲያካትት ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑም ሆነ የመምሪያዎችና የአገልግሎቶች የሥራ ዕቅዶች እና መርሐ ግብሮች እንዲሁም የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዝግጅትን በማስተባበርና በማጠናቀር የተሟላ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ወቅታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ያደርጋል፣ ለውሳኔ ያቀርባል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን ያዘጋጃል እቅዶችንም ለማስፈፀም በሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የንብረት መጠን ላይ ጥናት በማድረግ ኮሚሽኑ ሊገጥመው የሚችለውን ችግር እንዴት መወጣት እንዳለበት መፍትሄ ይጠቁማል፡፡ 

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ሌሎች ዝርዝር ተግባራት መካከል፡- 

በዕቅድና ኘሮግራም አወጣጥና ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ኮሚሽነሩን፣ ም/ኮሚሽነሩንና ዳይሬክተሮችን ማገዝ እና ማማከር፣
የኮሚሽኑን የሥራ ዕቅዶችና ሪፖርቶችን ማጠናቀር፣ ማዘጋጀት፣ ለውሳኔ አመች በሆነ መልክ ለከሚሽነሩ ማቅረብና ማማከር፣
የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ እንደመረጃ ማዕከል ሆኖ ማገልገል፣
የኮሚሽኑን መሠረታዊ መረጃዎችን ማጠናቀርና ለመረጃነት ዝግጁ ማድረግ፣
በኘሮጀክቶች ዝግጅት ድጋፍ ማድረግና ኘሮጀክቶችን ማዘጋጀት፣
የኮሚሽኑ ስትራቴጅክ እቅድ እንዲዘጋጅ ማስተባበር/ የመሪነቱን ሚና መጫወት/ እና የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄድ ይገኙበታል፡፡

የክልል ግንኙነት ጉዳይ ጽ/ቤት 

የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለክልሎች አስፈላጊ የምክርና የድጋፍ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 433/97 በአንቀፅ 7 15 ላይ ተደንግጓል፡፡ ኮሚሽኑም ይህን ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልክ መወጣት ይችል ዘንድ የክልል ግንኙነት ጉዳይ ጽ/ቤት አቋቁሟል፡፡ 

የጽህፈት ቤቱ ተጠሪነት ለምክትል ኮሚሽነሩ ሲሆን ለክልሎች ከሚያደርገው ድጋፍ መካከል የየራሳቸው የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና አካላት እንዲያቋቁሙና በተገቢው መምራትና ማስተዳደር እንዲችሉ እንዲሁም የክልል ኮሚሽኖች በተለያየ ወቅት የሚያቀርቧቸውን የድጋፍ ወይም የትብብር ጥያቄዎችን አግባብነት በመገምገም ተገቢ መልስ እንዲያገኙ ማስቻል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑ አካላት ከክልል ኮሚሽኖች ጋር በጋራ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራትን በማቀናጀት ተግባራዊ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ከክልል ኮሚሽኖች ጋር የመወያየትና የጋራ ዕቅድ የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሌላው የጽ/ቤቱ ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል የራሳቸውን ኮሚሽን ባላቋቋሙ ክልሎች መልካም ሥነምግባርን ከማስፋፋት፣ ሙስናን ከመከላከልና የሙስና ወንጀልን ከመመርመር አንፃር ኮሚሽኑ ስለሚያደርገው ድጋፍ የማጥናት፣ የማስወሰን፣ ተግባራዊነቱን የመከታተል እና የክልል ኮሚሽን ሠራተኞች በውጭ አገር ሥልጠና ወይም ልምድ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ተግባራትን ማከናወን ለጽ/ቤቱ የተሰጠ ሌላው ተግባር ነው፡፡

ለክልል ኮሚሽኖች ስለሚሰጥ ድጋፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ በየወቅቱ የማቅረብና ሲወሰንም ተግባራዊነቱን የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ለዚሁ ለክልል ጉዳይ ጽ/ቤት ሲሆን ለክልል ኮሚሽኖች የሚሰጠው ድጋፍ እና የሥራ ትብብርም በአብዛኛው ሥልጠና በመስጠት፣ በምክር አገልግሎት፣ በጋራ የትብብር ሥራዎች በመሳተፍ እና በአንድ ክልል የተገኘ ልምድን ወደሌላው በማስተላለፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡