News
The profile of the FEAC
Major objectives of FEAC
Amendment of the Proclamation
The revised establishment proclamation
The revised procedural proclamation
Directives and regulations
Principles and values
Annual Report
Publications
Vacancies
Contact Us
 proclamation pdf

1      ክቡር ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን መልዕክት

2      መግቢያ

3   ሙስና በኢትዮጵያ

    3.1 የሙስና ትርጉም

    3.2 የሙስና መገለጫዎች

    3.3 የሙስና ታሪካዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ

    3.4 የሙስና መንስኤዎ

    3.5 ሙስና የሚያስከትላቸው ጉዳቶች

    3.6 የሙስና ሁኔታ በኢትዮጵያ

    3.7 ለሙስና የተጋለጡ ዘርፎች

 

ቀጣይ አንድ

   ክቡር ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን መልዕክት

የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን (....) እና የስራ እንቅስቃሴዎቹ

የክቡር ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን መልዕክት

«የፀረ-ሙስና ትግሉ ዋነኛ ተዋናይ ህብረተሰቡ ነው!»

በአሁኑ ጊዜ ሙስና ከታላላቅ አለም አቀፍ ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስአት ግንባታ ሂደቶችን በሚያደናቅፍበት ደረጃ ላይ   ባይሆንም ሙስና በኢትዮጵያ ውስጥም ችግሮችን እየፈጠረ መገኘቱ ግልፅ ነው፡፡ ይህን አደጋ በመገንዘብ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የፌደራል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን (ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ) ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም በማቋቋም የፀረ-ሙስና ትግሉን በፌደራል ደረጃ እንዲያስተባብርና እንዲመራ አድርጓል፡፡

«ሳይቃጠል በቅጠል» እንዲሉ ሙስናን ከመስፋፋቱ በፊት በእንጭጩ መግታት በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መገኘቱ ግልፅ ነው፡፡ በፌደራል ደረጃ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ከዘጠኙ ክልሎች ሰባቱ የየራሳቸውን የስነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች በማቋቋም ሙስናን በአገር ደረጃ ለመከላከልና ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፆ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡

የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን የማስፋፋት፣ ሙስናን አስቀድሞ የመከላከል፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን የመመርመርና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ የማቅረብ አላማዎችን አንግቦ የተቋቋመው የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ የተጠቀሱትን አላማዎቹን ለማሳካት ባደረገው እንቅስቃሴ አበረታች ውጤቶችን አግኝቷል፡፡

ኮሚሽኑ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም እንዲሁም በፊት ለፊት የስልጠና ፕሮግራሞቹ አማካኝነት የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን ሰጥቷል፡፡ ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችንና ቀዳዳዎችን በመድፈን ሙስናን አስቀድሞ ለመከላከል ኮሚሽኑ ባደረገው ጥረት በ160 የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የአሰራር ስራአቶችን በመፈተሸ የማስተካከያ እርምጃዎችን ለየመስሪያ ቤቶቹ ከማቅረቡም በላይ ያቀረባቸውን የማሻሻያና የእርምት እርምጃዎች አፈፃፀምም ሲከታተል ቆይቷል፡፡

የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ጥፋተኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ ባደረገው እንቅስቃሴ ኮሚሽኑ ከ1,500 በላይ የሙስና ወንጀሎችን መርምሮ 520 የሚጠጉ ሙሰኞች ከ3-21 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ አድርጓል፡፡ በተለይም በመዲናችን በአዲስ አበባ ከመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ የተፈጸመውን ቅጥ ያጣ ወረራ ለመግታት ባደረገው ባለብዙ ፈርጅ ጥረት  ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ እነዚህ ተግባራት በማስተማር ሙስናን በመከላከል እና ህግን በማስከበር ረገድ የተከናወኑ ነበሩ፡፡ ከመሬት ጋር በተያያዘ በተደረጉ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴዎች ከ1,639,116.24 ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ያለውና ከ2.5 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የከተማ ቦታ48 ቤቶችና ድርጅቶች እንዲሁም 61 ተሽከርካሪዎች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግደዋል፡

ወቅቱ አገራችን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች ያለችበት ወቅት ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ይህ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነትና ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህን ቀጣይነት ለማረጋገጥ መከናወን ከሚገባቸው ወሳኝ ተግባራት መካከል ሙስናን በጽናትና በቁርጠኝነት መታገል አንዱ መሆኑን መንግስታችን ያምናል፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት አገራችን ለጀመረችው የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠል የፀረ-ሙስና ትግሉ የሚኖረውን ድርሻ በመገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

አገራችን ሙስናን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ጥረቶች እያደረገች ብትቆይም አንዳንድ የውጭ ተቋማት በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለችውን ጥረትና ያገኘችውንም ውጤት ለማሳነስ ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የሙስና ሁኔታ የልማት እንቅስቃሴያችንም ሆነ የዴሞክራሲያዊ ስራአት ግንባታችንን በሚገታበት ደረጃ ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አስፈላጊውን ጥረት ካላደረግን ወደፊት ተስፋፍቶ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስራአታችን እንቅፋት ከሚሆንበት ደረጃ ላይ አይደርስም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት ሙስናን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመግታትና እንዳይስፋፋ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ እያደረገ የሚገኘው፡፡

የመንግስት ቁርጠኝነትና የዜጎችም ተሳትፎ ታክሎበት በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ እያደረግነው ያለው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍሬ እያፈራ እንደሚገኝ እንገነዘባለን፡፡ ህብረተሰቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳትፎውን እያሳደገና ከኮሚሽኑ ጋር ተባብሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሕብረተሰቡ ራሱ በስፋት ያልተሳተፈበት የፀረ-ሙስና ትግል ሊሰምር እንደማይችል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተገንዝቧል ለማለት ይቻላል፡፡ ባጠቃላይ ባለፉት አመታት በተደረገው ጥረት የፀረ-ሙስና ትግሉን ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መድረኮችን በማቋቋም የባለድርሻ አካላትን የተደራጀ ተሳትፎ በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ ከሚዲያ ተቋማትና ማህበራት፣ ከሐይማኖት ድርጅቶች፣ ከብዙሐን ማህበራት፣ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ በህግ ልዕልና ዙሪያ ከሚሰሩ ማህበራት፣ሙስናን መዋጋትን እንደ አንድ አላማቸው አድርገው ከያዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሙያ ማህበራት ጋር በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ የጋራ መድረኮችን አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

የተጠቀሱትን የጋራ መድረኮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ማቋቋማችን መልካም ጅምር ቢሆንም ሁሉም አካላትና ወገኖች የሚሳተፉበት፣ አንድ አገራዊ ራዕይ የያዘና ከዚህ የሰፋ መድረክ የመፍጠርን አስፈላጊነት ግን የሚተካ አይደለም፡፡ ስለሆነም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት አንድ አገር አቀፍ ጥምረት መመስረትን አስፈላጊ አድርጐታል፡፡ መድረኩ መላው ህብረተሰብ በፀረ-ሙስና ትግሉ በንቃት እንዲሳተፍ ከማስቻሉም በላይ በፀረ-ሙስና ትግሉ የጋራ ራዕይና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ያስችለዋል፡፡ ለዚህም ነው ኮሚሽኑ ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር አገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት እንዲመሰረት ያደረገው፡፡

ኮሚሽኑ ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱትን አበረታች እንቅስቃሴዎች ቢያደርግም ሙስና መቸም ቢሆን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስራአት ግንባታችን እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ያምናል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ አመታት የአፈፃፀም ብቃቱንና ውጤታማነቱን ከፍ ለማድረግ መሰረታዊ የአሰራር ስርአት ጥናት (BPR) በማካሄድ ወደ ሙሉ ትግበራ ገብቷል፡፡ መሰረታዊ የአሰራር ስራዓት ጥናቱ ወደ ተግባር እየተሸጋገረ ሲሄድ የቆመላቸውን አላማዎች በከፍተኛ ደረጃ በማሳካት የፀረ-ሙስና ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር እሙን ነው፡፡ ይህንንም ስል ህብረተሰቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ የሚኖረው ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመዘንጋት አይደለም፡፡ ኮሚሽኑ እስካሁን ያስመዘገባቸው ውጤቶችም ቢሆኑ በህበረተሰቡ ተሳትፎ የተገኙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ለመላ ህብረተሰቡ በማስተላልፈው አጭር መልዕክቴ «እናንተ የትግላችን ወሳኝ ሐይል በመሆናችሁ ትግላችን የላቀ ውጤት ያስመዘግብ ዘንድ በፀረ-ሙስና ትግሉ ተሳትፏችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ» እላለሁ፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመታገል ሙስናን መግታት ይቻላል፡፡ አዎ፣ ይቻላል!

2 .    መግቢያ

ኮሚሽኑ ይህን መጽሔት ያዘጋጀው የፀረ-ሙስና ትግሉ የጀርባ አጥንት የሆነው ዜጋም ሆነ ሌሎች አካላት በአገራችን እየተካሄደ ስላለው የፀረ-ሙስና ትግል እንዲሁም ስለ ኮሚሽኑ አላማዎችና እንቅስቃሴዎች በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ለማስቻል ነው፡፡ መላውን ህብረተሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በፀረ-መስና ትግሉ በንቃት መሳተፍ አለባቸው ስንል እነዚህ ወገኖች ይህን ግዴታቸውን በአግባቡ ይወጡ ዘንድ ስለ አገራዊው የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ መረጃ የመስጠት ግዴታም በኛ ላይ እንደሚወድቅ በመረዳት ጭምር ነው፡፡ በተጨማሪም በበቂ መረጃ ላይ ተደግፎ የሚከናወን ተግባር ውጤታማነት ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህችን አጠቃላይ መረጃ የምትሰጥ መጽሔት ለማዘጋጀት ችለናል፡፡

በቀጣዮቹ አመታት አሁን እያስመዘገብን ከለነው የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላትን የፀረ-ሙስና ተሳትፎ ከፍ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽኑ በጽናት ያምናል፡፡ ስለሆነም የዚህን ጉዳይ አስፈላጊነት በተመለከተ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ህትመቶችንና ሌሎች የሚዲያ ውጤቶችን አዘጋጅቶ ማሰራጨት ጠቃሚ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በነዚህ ህትመቶችና የሚዲያ ውጤቶች አማካኝነት በኢትዮጵያ የሙስና ሁኔታ ምን እንደሚመስል፣ ስለሙስና ምንነት መገለጫውን፣ መንስኤዎች፣ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶችና የመከላከያ ስልቶቹን በተመለከተ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም ህብረተሰቡ እየተካሄደ ስለሚገኘው አገራዊ የፀረ-ሙስና ትግል ወቅታዊ መረጃ ማግኘቱ በፀረ-ሙስና ትግሉ ተገቢ ድርሻውን እንዲወጣ እንደሚያስችለው እንረዳለን፡፡ አገሪቱ ሙስናን በመታገልና በመከላከል ረገድ ስላሏት ፕሮግራሞችና ስለምትከተላቸው መርሖችም ህብረተሰቡ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጽሄቷ በሙስና ዙሪያ ጥናትና ምርምር ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች በመረጃ ምንጭነት ልታገለግል እንደምትችል ይታመናል፡፡  

በዚህ መጽሔት ውስጥ የተካተቱት መረጃዎች የተሰበሰቡት ከኮሚሽኑ የተለያዩ የሥራ ሂደቶችና ክፍሎች፣ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከፀረ-ሙስና አዋጆችና ሕጎች፣ ከኮሚሽኑ ረቂቅ የፀረ-ሙስና ፖሊሲ፣ ከኮሚሽኑ የሥነምግባር ትምህርት ማኑዋል፣ በሙስና ላይ ከተካሔዱ ጥናቶችና ከሌሎች ምንጮች ነው፡፡ ሙስናን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ለመከላከልና ለመዋጋት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም የፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮን ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ሙስናን በሶስት ዋና ዋና መንገዶች (three-pronged approaches) መታገሉን ቀጥሏል፡፡ እነሱም፡-

v  የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርትን በማስፋፋትና ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ በመፍጠር፣

v   የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሰራርን አስቀድሞ በመከላከል

v   ሙስና ተፈፅሞ ሲገኝ ደግሞ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግና በሙስና የተገኘ ሐብት ለትክክለኛ ባለመብቱ ማለትም ለህዝብ እንዲመለስ ማድረግ ናቸው፡፡

ባለፉት 9 አመታት የተጠቀሱትን ዓላማዎች በማንገብ ኮሚሽኑ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ያስመዘገባቸውን አበረታች ውጤቶች መፅሔቷ አካታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች፣ ያጋጠሙትን ችግሮች፣ ተገልጋዮች በተደጋጋሚ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች እንዲሁም የተሰጡትን መልሶች በተመለከተ መፅሔቷ አስፈላጊ መረጃዎችን ይዛለች፡፡ መፅሔቷን በተመለከተ ያለዎትን አስተያየት በሚከተሉት አድራሻዎች ሊሰጡን ይችላሉ፡፡

የፌደራል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን

v       ስ.ቁ፡ 251-115-503231

v       ፖ. ሳ. ቁ፡ 34798/9

v       ፋክስ፡ 251-115-503190

v       ኢ-ሜይል፡ feacedu@ethionet.et

3 ሙስና በኢትዮጵያ

3.1 የሙስና ትርጉም

ሙስና በተለያዩ ጸሐፍትና ተመራማሪዎች የተለያዩ ትርጉሞች ይሰጡታል፡፡ ይሁንና በአለም አቀፍ ደረጃ በአመዛኙ ተቀባይነት ያገኘውና በኮሚሽኑ ረቂቅ የፀረ-ሙስና ፖሊሲ ላይ የሰፈረው የሙስና ትርጉም እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡

ሙስና ማለት በአንድ አካል ወይም በአባላቱና ኃላፊዎቹ አንድን ተግባር የመፈፀም ወይም ያለመፈፀም ሁኔታ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጽእኖ ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት ሲባል ውለታ፣ የተስፋ ቃል፣ እጅ መንሻና ጥቅማጥቅም መስጠት ወይም መቀበል፤ በቃላት ወይም ከዚህ ውጭ በሆነ ሁኔታ ዛቻ ወይም ማስፈራራት ማድረግ እንዲሁም ስልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ተጽእኖ ማሳደር ነው፡፡

3.2 የሙስና መገለጫዎች

በ1993 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጋር በመተባበር ባካሄደው የሙስና ቅኝት (survey) ውስጥ እንደተገለፀው እንዲሁም በሌሎች ምንጮች መሰረት ማታለል፣ ምዝበራ፣ ማጭበርበር፣ በሥልጣን ያለ አግባብ መገልገል፣ በዝምድናና በወዳጅነት መስራት (አድልዎ)፣ ስርቆት፣ እምነት ማጉደል፣ ሰነድ መደለዝ እና ጉቦ መስጠትና መቀበል ዋና ዋናዎቹ የሙስና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መገለጫዎች መካከል አብዛኛዎቹ በኮሚሽኑ የእስከአሁን የሥራ እንቅስቃሴ በተግባር የታዩ ናቸው፡፡ በእማኝነት የኮሚሽኑን የ2000 ዓ.ም ስታቲስቲካዊ መጽሔት መመልከት ይቻላል፡፡

3.3 የሙስና ታሪካዊ ሁኔታ በኢትዮጵ

በኢትዮጵያ የሙስናን ታሪካዊ ሁኔታ መለስ ብለን ስንመለከት በግልፅ የሚታወቁት የሙስና ወንጀሎች ሁሉ የመሸፋፈኛ ስሞች ተሰጥቷቸው እንደ ወንጀል የማይቆጠሩበት ሁኔታ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ ጉቦ በአፄ ሐይለስላሴ ዘመን እንደ ጉዳይ ማስፈፀሚያ ወይም እጅ መንሻ (መታያ) እንጅ እንደ ወንጀል የማይቆጠርበት ሁኔታ ነበር፡፡ መታያው የሚሰጠው ያልተገባ ጥቅም በተለይ ሹመትንና የመሳሰሉትን ለማግኘት ሆኖ በግልፅና በአደባባይ ተመን ወጥቶለት የሚከናወን ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወንጀል የሚቆጠርበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ፃሐፍት «መታያ» በቤተመንግስት ውስጥ ራሱን የቻለ ቢሮ ተደራጅቶለት ተግባራዊ ሲሆን መቆየቱን ይገልፃሉ፡፡ መታያ የሚሰጡ ሰዎች ሹመት ፈላጊዎች ካልሆኑ ምን እንደሚፈልጉ ይጠየቁና ጉዳያቸው ይፈፀምላቸው እንደነበር ከታሪክ መዛግብት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በዝምድናና በወዳጅነት መስራት ደግሞ «ዘመድን መርዳት» የሚል ስያሜ ተሰጥቶትና እንደወንጀል ሳይቆጠር ይከናወን እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንዳንዶቹ ባለስልጣናት ዘመዶቻቸውን በቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች ላይ አስቀምጠው የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሐብት በግልፅ ለራሳቸው ጥቅም ያውሉ እንደነበር አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ከአፄው ዘመን በኋላ ሥልጣን የያዘው ደርግም ቢሆን ሙስናን አባባሰው እንጂ አልቀነሰውም፡፡ በተለይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ እጅግ የወረደበት፣ የመንግስት ሰራተኞች ሥነምግባር ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሸረሸረበት፣ የህግ የበላይነት የጠፋበትና ሰብአዊ መብቶች የሚረገጡበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህና ሌሎች የግልፅነትና የተጠያቂነት መርህን የሚጎዱ አሰራሮች በደርግ ዘመን ሙስና የሰፈነበት አሰራርን አባብሰውት እንደነበር ግልፅ ነው፡፡   

ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ግን የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራርን በፅናት የሚደግፍ፣ ሙስናን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመዋጋት የሚያስችሉ ተቋማትንና የተለያዩ ህጎችን አውጥቶ በቁርጠኝነት የሚንቀሳቀስ ስርአት በመፈጠሩ ሙስና ህጋዊ ሽፋን ተሰጥቶት እንደተፈለገ የማይፈፀምበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ሙስናን ዘለቄታ ባለው መንገድ ለመዋጋትና ለመከላከል እንደሚያስችል ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እስከዛሬ የተገኙት አበረታች ውጤቶችም ይህን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስናን ለመዋጋትና ለመከላከል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ስርአት ውስጥ ስለምንገኘ እንዳለፉት ስርአቶች ቅጥ ባጣ መልኩ ለሙስና የተጋለጥን ነን ለማለት አይቻልም፡፡

3.4 የሙስና መንስኤዎች

 

በዘርፉ ጥናት በማድረግ የተሰማሩ ምሁራን እንደሚስማሙበት የሚከተሉት ሁኔታዎች በኢትዮጵያ በሙስና መንስኤነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር በሚፈለገው ደረጃ አለመጎልበት፣ ተቋማዊ ቁጥጥር በሚፈለገው ደረጃ አለመጐልበት፣ ድህነት፣ ሙስናን የሚያበረታቱ ጎጂ ባህሎች መኖር፣ የፕራይቬታይዜሽን ሂደት፣ በሚፈለገው መጠን ያልተገነባ የፋይናንስ ሰርዓት፣ በኦዲትና በአካውንቲንግ ዘርፎች የሚታየው የእውቀትና የክህሎት ማነስ እንዲሁም የመልካም ሥነምግባር እሴቶች መሸርሸር በዋና ዋና መንስኤነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከጊዜ ጊዜ መሻሻል እየታየበት ቢመጣም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚታየው የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘት በሙስና መንስኤነት የሚጠቀስ ነው፡፡

3.5 ሙስና የሚያስከትላቸው ጉዳቶች

 በአፄውና በደርግ ዘመናት ሙስና እየከፋና መንግስታዊ መዋቅሮቻቸውን እያዳከመ መጥቶ በመጨረሻ የስራአቶቹን ግብዓተ-መሬት ለማፋጠን አንዱ ምክንያት እንደነበር በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ሙስና ለስርአቶቹ ፍፃሜ አንዱ ምክንያት ከመሆኑ ጋር እድገትና ልማትን በማቀጨጭ፣ ድህነትን በማባባስ፣ ማህበራዊ አለመረጋጋትን በመፍጠርና የህግ የበላይነትን በማዳከም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሙስና የሚከተሉትን ጉዳቶች እንደሚያደርስ ይታመናል፡፡

v      ለኢኮኖሚ እድገት የተነደፉ የልማት ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ የጎላ ጥቅም በማይሰጡ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲተኩ ሊያደርግ ይችላል፡፡

v      የመንግስት በጀት ቅድሚያ ሊሰጠው በሚገባ ተግባር ላይ ሳይሆን ዝቅተኛ ትኩረት በሚሰጠው ዘርፍ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

v      የግብር አሰባሰብ ስርአትን በማዛባት መንግስት ከግብር ሊያገኝ የሚገባውን ገቢ እንዲያጣ ያደርጋል፡፡ ይህም ልማትን በማምጣት ረገድ የመንግስትን አቅም በእጅጉ ይጎዳል፡፡

v      አዳዲስ ኢንቬስተሮችን በማሸሸትና ያሉትንም በማዳከም ሁለንትናዊ የአገር እድገትን ያጓትታል፡፡

v      የፍጆታ እቃዎችን መጠንና ጥራት በመቀነስ እንዲሁም የምርትና የአገልግሎት ዋጋ ያለ አግባብ እንዲንር በማድረግ ህዝብን ለከፋ የኢኮኖሚ ችግር ይዳርጋል፡፡

v      የህግ የበላይነትን ይሸረሽራል፡፡

v      የወገንተኝነትንና አድሏዊ አሰራረርን ያሰፍናል፡፡

v      ሕዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ ያደርጋል፡፡

v      አገራዊ አለመረጋጋትን ይፈጥራል፡፡

v      የአካባቢ ብክለትን ያስከትላል፡፡

አልፎ ተርፎም ለእርስበርስ ጦርነት መንስኤ ይሆናል፡፡ 

3.6 የሙስና ሁኔታ በኢትዮጵያ

 

በኢትዮጵያ የሙስናን ሁኔታ ለማወቅ የተወሰኑ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በ1993 ዓ.ም በፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የተካሄደው የሙስና ቅኝት (survey) ከዚህ አንፃር ተጠቃሽ ነው፡፡ ጥናቱ ሙስናን (ቢያንስ የጥናቱ ውጤት ይፋ በሆነበት ጊዜ) ከዋና ዋና የአገሪቱ ችግሮች አንዱ ወደሚሆንበት ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የዚህ ጥናት ውጤት አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል አያንፀባርቅም ይላሉ፡፡ በእነዚህ ወገኖች እምነት ጥናቱ ከተካሔደ በኋላ ሁኔታዎች በእጅጉ ተቀይረዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለውን ሁኔታ በዚህ ጥናት ላይ ተመስርቶ መግለፅ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽንስ ኮርፖሬሽን፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሐይል ኮርፖሬሽንና በመሳሰሉት አገልግሎት ሰጭ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛና የሙስና ችግር እንዳለ ጠቁሟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እነዚህን በመሳሰሉት ድርጅቶች ውስጥ ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ተቋማቱ ፈፅሞ የሙስና ችግር የለባቸውም ባይባልም በጥናቱ በተመለከተው መጠን ችግሩ አሁንም አለ ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማትም ሆነ በመሰል የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራርን ለመዘርጋት የተደረጉ ጥረቶች ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት የማይናቅ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ይታመናል፡፡

ከዚህም በላይ ለጥናቱ የተወሰዱት ናሙናዎች (samples) ብዛትና ወካይነት የሚፈለገውን ያህል አይደለም በሚል የጥናቱን ተአማኒነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ አንዳንድ ወገኖች አሉ፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ድርጅቶች ከቅርብ አመታት ወዲህ ያጠኗቸው ጥናቶች በተሻለ ደረጃ የኢትዮጵያን የሙስና ሁኔታ ለማመልከት ይችላሉ ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የተለያዩ ወገኖች በኢትጵያ የሙስና ሁኔታ ላይ የደረሱበትን ድምዳሜ ማቅረቡ በመረጃ ሰጭነቱ ጠቃሚ ነው በሚል እንዳለ አስቀምጠነዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ባወጣው ሪፖርት (እ.ኤ.አ የ2004 ዓ.ም ሪፖርት ገጽ 11) ሙስና በኢትዮጵያ በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁሞ ይህም በመሆኑ አገሪቱ ለኢንቨስትመንት አመች መሆኗን አስቀምጧል፡፡ በዚህ ሪፖርት አገላለጽ «ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ከሚገኙ አገራት (LDCs) ለየት ባለ ሁኔታ ሙስና የሌለባት አገር ናት»፡፡ ሌላው «በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ» የተዘጋጀ የጥናት ሪፖርት (እ.ኤ.አ 2008፣ ገጽ 49) ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሙስናን በመዋጋት ረገድ እየተሳካለት መምጣቱን ጠቁሟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአለም ባንክ የአገራትን ለንግድ አመችነት ደረጃ አስመልክቶ ባዘጋጀው ሪፖርት ኢትዮጵያን ከበርካታ አገራት በተሻለ ደረጃ ያስቀመጣት ሲሆን ይህን ደረጃ የሰጠው ሙስና በአገሪቱ ያለበትን ዝቅተኛ ደረጃ ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ሙስናን በመዋጋትና መልካም አስተዳደርን በማስፋፋት ስራ ላይ የተሰማራውና መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው «ግሎባል ኢንተግሪቲ» የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2006 ባዘጋጀው አገራት ሙስና በሚመለከት ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ ሪፖርት ኢትዮጵያ ሙስና በአነስተኛ መጠን ከሚታይባቸው ጥቂት የአፍሪካ አገራት ተርታ የምትሰለፍ መሆኗን አመልክቷል፡፡ በኢትዮትዮጵያ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ቻፕተር በሙስና ላይ እ.ኤ.አ በ2008 ባካሔደው መሰረታዊ ጥናት አብዛኛዎቹ በጥናት ቡድኑ መጠይቅ ተበትኖላቸው ሐሳባቸን የሰጡ ኢትዮጵያውያን አሁን እየተካሔደ ያለው አገራዊ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በዚህ መልኩ ተጠናክሮ ከቀጠለ በቀጠዮቹ አመታት በኢትዮጵያ ያለው የሙስና ሁኔታ እንደሚቀንስ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአለም ባንክ በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ስላለው ሙስና አስመልክቶ እ.ኤ.አ በጁን 2008 ባወጣው የጥናት ሪፖርት ሙስና በግንባታው ዘርፍ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ይህ ሪፖርት እንደሚያትተው በግንባታው ዘርፍ ሙስና ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ አንዳንድ ወገኖች የያዙት «በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሙስና ስር ሰዷል» የሚለው አመለካከትና የጥናቱ መደምደሚያ በእጅጉ የሚለያዩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

ባጠቃላይ የተጠቀሱት ሪፖርቶችና ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ተቋማዊና ስር የሰደደ ሙስና የለም፡፡ ከተጠቀሱት ምንጮች በተጨማሪ ኮሚሽኑ ላለፉት 9 አመታት የሙስና ወንጀሎችን ሲመረምርና ወንጀለኞቹንም ለህግ ሲያቀርብ እንዳስተዋለው በኢትዮጵያ አለ የሚባለው ሙስና ተቋማዊ በሆነ መልኩ (systemic) የሚገለፅ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በትላልቅ የሙስና ወንጀሎች የሚፈረጁ ድርጊቶች አላጋጠማትም ባይባልም ብዙዎቹ ኮሚሽኑን ያጋጠሙት የሙስና ወንጀሎች በአነስተኛ የሙስና ወንጀልነት (Petty corruption) የሚታዩ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ሙስናን በተመለከተ ምንም አይነት ችግር የለምና ወደፊትም ቢሆን እጆቻችን አጣጠፈን መቀመጥ አለብን ማለት አይደለም፡፡ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን በሚያደናቅፍ ደረጃ ባይሆንም እየታዩ ያሉ የሙስና ችግሮችን እየተዋጋንና እየታገልን የልማታችንን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ጥረታችንን በዚህ መልኩ ካልቃኘነው ሙስናው ወደ ከፍተኛ ችግርነት የማይሸጋገርበት ምክንያት የለም፡፡

3.7 ለሙስና የተጋለጡ ዘርፎች

 አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ለሙስና ተጋላጭ ከሆኑ ዘርፎች መካከል የፋይናንስ ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት ቤቶች አሰጣጥና አስተዳደር፣ በመሬት አስተዳደር፣ በስልክና በመብራት አገልግሎት አሰጣጥ፣ በፈቃድ ሰጭ ድርጅቶች፣ በታክስ መሰብሰብና ከፍተኛ ግዥ የሚያከናውኑ ተቋማትና ድርጅቶች ለሙስና የተጋለጡ መሆናቸውን አንዳንድ መለስተኛ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኮምፒዩተርና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚፈፀም የሳይበር ወንጀል (cyber theft) በፋይናንሱ ዘርፍ ላይ አንዳንድ ችግሮችን እያስከተለ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ የምርመራ ሒደቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ቀጣይ አንድ