News
The profile of the FEAC
Major objectives of FEAC
Amendment of the Proclamation
The revised establishment proclamation
The revised procedural proclamation
Directives and regulations
Principles and values
Annual Report
Publications
Vacancies
Contact Us
 proclamation pdf

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምሥረታ እና እንቅስቃሴዎቹ

 

3   የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አመሠራረት

    የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ እና የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓት እና ማስረጃ ህግ እንዲሻሻሉ ያስፈለገባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች

4.1 በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተደረጉ ዋና ዋና ማስተካከያዎች

4.2 በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ላይ የተደረጉ ዋና ዋና ማስተካከያዎች

ቀጠይ ሁለት

3.  የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን አመሠራረት

    ከዚህ በላይ እንደተገለፀው ሙስና በአገሪቱ ውስጥ ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት እ.ኤ.አ በ2ዐዐ1 የተካሄደው ጥናት ችግሩ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ እንደቆየ ያስገነዝባል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሙስናን ለመከላከል ጥረት የሚያደርግ ተቋም ሳይመሰረት መቆየቱ ደግሞ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንዲመጣ መንገድ ከፍቶ ቆይቷል፡፡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት የሥነምግባር ትምህርትን በማስፋፋት ሙስናን ለመሸከም ፈቃደኛ ያልሆነ ህብረተሰብ መፍጠር፣ ሙስናን መከላከል፣ የሙስና ወንጀልን መመርመርና ሙስና እንደተፈፀመ ጥርጣሬ ሲኖር ክስ በመመስረት ሙሰኞች ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ዓላማ የያዘውን የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ለማቋቋም የሚያስችል መሠረት ተጣለ፡፡

    ሙስናን ለመዋጋት በመካሄድ ላይ ያለው እንቅስቃሴ መንግሥት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ገጽታዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት በማካሄድ ላይ ለሚገኘው ጥረት ወሳኝ ድርሻ ያለው እንደመሆኑ መጠን የፀረ-ሙስናውን እንቅስቃሴ ተግባራዊ ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነበር፡፡ በመሆኑም መንግሥት በአምስት ዘርፎች ላይ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ኘሮግራም ነድፎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሥነምግባር ማሻሻያ ንዑስ ኘሮግራም ነው፡፡ በሥነምግባር ማሻሻያ  ንዑስ ኘሮግራም ሥር የፀረ-ሙስና ትግሉን ተፈፃሚ ለማድረግ መንግሥት የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን የማቋቋም አስፈላጊነት ተገነዘበ፡፡ ይህም እርምጃ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተከናወነ ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የነበረው ተግባር ኮሚሽኑን ለማቋቋም የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማከናወን ነበር፡፡ ከእነዚህ ቅድመ ዝግጅቶች መካከል ሥልጠናዎችን ማካሄድ፣ በዘርፉ ያለውን አለም አቀፍ ተሞክሮ በማጥናት ጠቃሚ ሃሳቦችንና ልምዶችን መውሰድ፣ በችግሩ ስፋትና ሊወሰዱ በሚገባቸው መፍትሄዎች ዙሪያ ጥናት ማካሄድ፣ የኮሚሽኑን ድርጅታዊ መዋቅር ማዘጋጀት እና ብሔራዊ የፀረ-ሙስና ሰርቬይ ማካሄድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ኮሚሽኑን ለማቋቋም በነበረው ቅድመ ዝግጅት ላይ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ አካላት ንቁ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኃይማኖት ድርጅቶች፣ የሙያ ማህበራት፣ የመንግሥት /ቤት ወኪሎች እና የሚዲያ ተቋማት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ተግባራዊ ሂደቶች ከተጠናቀቁ በኊላ የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በግንቦት 1993 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ 

         ኮሚሽኑ ለተወሰኑ ዓመታት በአዋጅ የተሰጡትን ተግባራት ሲያከናውን ከቆየ በኊላ በሥራ ሂደት የታዩ ሁኔታዎች የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅና የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነስርአት እና ማስረጃ ህግ መሻሻልን አስፈላጊ አድርገውታል፡፡

4 የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ እና የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓት እና ማስረጃ ህግ እንዲሻሻሉ ያስፈለገባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች

ኮሚሽኑ አዋጆቹን መሠረት አድርጐ በመጀመሪያዎቹ አራት ዓመታት ሲያከናውናቸው ከቆያቸው ተግባራት በአገኘው ተሞክሮ በአዋጆቹ ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባ የተረዳበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀረፀው የኮሚሽኑ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ የአዋጆቹ መሻሻል አስፈላጊነት ተመልክቷል፡፡ እቅዱን መሠረት በማድረግና ሌሎችም ሁኔታዎችን በማገናዘብ አዋጆቹን ለማሻሻል በኮሚሽኑ ደረጃ ጥናት የተካሄደበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህን ጥናቶች መሠረት በማድረግና ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት አዋጆቹ በሕግ አውጭው አካል እንዲሻሻሉ ሆነዋል፡፡

ለአዋጆቹ መሻሻል እንደ አንድ ምክንያት የሚወሰደው የአገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በመሻሻሉና የኮሚሽኑንም አዋጆች ከዚህ ከተሻሻለው የወንጀል ህግ ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የሙስና ወንጀል ትርጉምን፣ የክስ ሂደቱንና የማስረጃ ጉዳይን ከወንጀል ሕጉ ጋር ማጣጣም ተገቢ ሆኖ መገኘቱም ለተደረገው ማሻሻያ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የዋስትና ጉዳይን፣ ንብረት የማገድና ሌሎች ግልፅ ያልሆኑ ድንጋጌዎችን ለማስተካከል፣ ኮሚሽኑ  ከሌሎች አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት በግልፅ ለማስቀመጥ እንዲሁም በሙስና ወንጀል የምርመራ ሂደት መረጃ ለማግኘት የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን ለማስወገድ የአዋጆቹ መሻሻል አስፈላጊ ሆኗል፡፡

የእነዚህ አዋጆች መሻሻል የኮሚሽኑን ሥራም ሆነ የፀረጠሙስና ትግሉን በተሻለ ሁኔታ እንደሚያግዝ ይታመናል፡፡ ከፖሊስ፣ ከፍ/ቤቶችና ከሌሎች መሰል አካላት ጋር የሚኖረንን የሥራ ግንኙነት ግልፅና የተሳካ እንደሚያደርጉት ይታመናል፡፡ የተሻሻሉትን አዋጆች ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ኮሚሽኑ ከአዋጆቹ ጋር የሚጣጣሙ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ማውጣት የአሠራር አቅጣጫዎችን መቀየስ አስፈላጊ በመሆናቸው በዚህ ረገድ አንዳንድ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የኮሚሽኑን ሠራተኞች የአስተዳደር ደንብ የማሻሻልና ከሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስነውን ደንብ የማዘጋጀት እና ሌሎች ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

4.1     በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተደረጉ ዋና ዋና ማስተካከያዎች

በነባሩ የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ማቋቋሚያ አዋጅ «ከባድ የሥነምግባር መጣስ ምንድን ነው»  ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁንና በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 መሠረት «ከባድ የሥነምግባር መጣስ ማለት አግባብ ባለው የሥነምግባር ደንብ መሠረት ከሥራ ሊያሰናብት የሚችል ጥፋት ነው፡፡» ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

ኮሚሽኑ በከባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ችግሩን ለመዋጋት እንዲያስችለው «ከባድ የሙስና ወንጀል» ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 9 መሠረት «ከባድ የሙስና ወንጀል» ማለት፣  

ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ባላቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የሚፈፀሙ ከፍተኛ የገንዘብ መጠንን ያካተቱ የሙስና ወንጀሎች ወይም፣

የመንግሥት ባለሥልጣንን የሚመለከቱ የሙስና ወንጀሎች ወይም፣

በአገር ሉአላዊነት፣ ኢኮኖሚ፣ ፀጥታ እንዲሁም በሕብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ የሙስና ወንጀሎች ናቸው፡፡

በነባሩ አዋጅ ውስጥ መሻሻል የተደረገበት ሌላው ነጥብ ደግሞ ከኮሚሽኑ ተጠሪነት ጋር የተያያዘው ነጥብ ነው፡፡ ቀደም ባለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነ ቢደነገግም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከምርመራ እና ከክስ ጋር ከተያያዙ ጉዳዮች ውጭም ቢሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍና መመሪያ እንዲሰጡ በር የማይከፍት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ተሻሽሎ በወጣው አዋጅ ላይ የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንቀጽ 4 ላይ «ኮሚሽኑ በሚመረምራቸው ወይም ክስ በሚመሰርትባቸው ወይም ክስ በመሰረተባቸው ጉዳዮች ላይ ከማንኛውም ሰው ወይም አካል ጣልቃ ገብነትና አመራር ነፃ ነው፡፡» በሚል የተቀመጠ በመሆኑ በግልጽ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ውጪ ኮሚሽኑ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ አመራርና ድጋፍ የሚያገኝበት ዕድል መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ዓላማውን ለማስፈፀም ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር ተባብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ተሻሽሎ በወጣው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ከተዘረዘሩት የኮሚሽኑ ዓላማዎች መጀመሪያ ላይ «አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር» የሚል ሐረግ እንዲካተትባቸው ተደርጓል፡፡

የተሻሻለው የኮሚሽኑ አዋጅ እልባት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ኮሚሽኑ የአሰራር ሥርዓታቸውን የሚያጠናቸው የመንግሥት /ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የኮሚሽኑን የእርምት አስተያየት ተግባራዊ ስለሚያደርጉበት ሁኔታ ነው፡፡

በነባሩ አዋጅ ኮሚሽኑ የመንግሥት መ/ቤቶችንና የልማት ድርጅቶችን የአሠራር ስርዓት  እያጠና «እንዲሻሻል በማድረግ ሙስናን የመከላከል» የሚለው ሐረግ በአንድ በኩል ኮሚሽኑ የሚያቀርበውን የመፍትሔ ሀሳብ ተጠኝ መስሪያ ቤቶች እንዲተገብሩ ይገደዳሉ የሚል ትርጓሜ ሲያመጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጠኝ መስሪያ ቤቶች በራሳቸው አሰራር ላይ የሚደረግ መሻሻል እራሳቸው አምነውበት ሊመጣ ይገባል፣ የማያምኑበትን ወይም ያልተቀበሉትን የማሻሻያ ሀሳብ እንዲተገብሩ ማስገደድ አይገባም የማለት እንደምታ ያዘለ በመሆኑ ከዚህ አንጻር የትኛውን አካሄድ መከተል እንደሚገባ በግልጽ በሚያስቀምጥ መልኩ ድንጋጌውን ማሻሻል አስፈልጓል፡፡

ስለሆነም፡-

·        ኮሚሽኑ የመንግሥት /ቤቶችንና የልማት ድርጅቶችን የአሰራር ሥርዓት በማጥናት ለሙስናና ለብልሹ አሰራር እንዳይጋለጡ አሰራሮቹ እንዲሻሻሉ ማሳሰብ የሚገባው እንደሆነ፣

·        ተጠኝው መ/ቤት አሰራሩ በሚያመጣው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት የሚመሰገንበት ወይም የሚጠየቅበት በመሆኑ ማሻሻያውን አምኖበት መተግበር እንደሚገባው፣

·        ነገር ግን በኮሚሽኑ አስተያየት ተጠኝው /ቤት ያለበቂ ምክንያት አሰራሩን ለማሻሻል ፈቃደኛ ካለሆነ ወይም ለማሻሻል ከዘገየ በሚመለከታቸው የበላይ አካላት/ እንደሁኔታው ከሥራ አመራር ቦርድ እስከ ተቆጣጣሪ ሚኒስቴር /ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት እስከ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ/ ተገቢ የሆነ እርምጃ ወይም ውሳኔ እንዲሰጥበት የማሳወቅና የማሳሰብ፣ በእነዚህ አካላት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ የመከታተል ኃላፊነት ባለው መልኩ የተሻሻለው አዋጅ ተስተካክሎ እንዲቀረጽ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ጐን ለጐን ኮሚሽኑ በዋነኛነት ከባድ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ላይ ማተኮር እንዲገባውና ይህን የመመርመር ስልጣንም እንደአስፈላጊነቱ በቅንጅት የሚሰራበትን ወይም ለሌላ አካል በውክልና የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና እንዲሁም ከባድ ያልሆኑ የሙስና ወንጀሎችን በሚመለከት ጠቅላላ ውክልና ለሌሎች የምርመራ አካላት ስለሚሰጥበት ሁኔታ በተሻሻለው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተካትቷል፡፡

ይህ የተሻሻለው የኮሚሽኑ አዋጅ በነባሩ አዋጅ ኮሚሽነሩን የሚያማክር አማካሪ ቦርድ እንዲቋቋም የሚደነግገውን አንቀጽ አላካተተም፡፡ ምክንያቱም በተሻሻለው አዋጅ የኮሚሽኑ የበላይ ተቆጣጣሪ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር ለኮሚሽኑ አጠቃላይ አመራር በመስጠትም ሆነ የስራ አፈጻጸሙን በመከታተል ከነባሩ አዋጅ በተሻለ መልኩ ስልጣን ስለአለው፣ እንዲሁም የተወካዮች ምክር ቤትም የኮሚሽኑን አሰራር የሚከታተልና የሚቆጣጠር በመሆኑና እነዚህ የመቆጣጠሪያና የመከታተያ ሥርዓቶች በቂ ስለሆኑ በተሻሻለው አዋጅ ላይ የአማካሪ ቦርዱ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም አዋጁ የኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላት ሙስናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሊጫወቱት ስለሚገባ ሚና ተጨማሪ አንቀጾችን በግልጽ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል በኮሚሽኑና በክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ተቋማት መካከል ቋሚ የግንኙነት መድረክ መፍጠር ሙስናን በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል አስፈላጊ በመሆኑ በኮሚሽኑና በክልል ተቋማት መካከል ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት በተሻሻለው አዋጅ አንቀጽ 25 ላይ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

4.2     በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ላይ የተደረጉ ዋና ዋና  ማስተካከያዎች

ከነባሩ የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ በተለየ ሁኔታ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ላይ በሰኔ 1996 በፀደቀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ውስጥ ተለይተው የተደነገጉትን የሙስና ወንጀሎች እና የሙስና ወንጀልን ትርጉም በሚያጣቅስ መልኩ በአዋጁ አንቀጽ ሁለት ላይ እንዲቀረጽ ሆኗል፡፡

በተጨማሪም የቀድሞው አዋጅ የአፈጻጸም ወሰኑ ተለይቶ ባለመቀመጡ ለተለያየ ትርጓሜ በር ከፍቶ የቆየ በመሆኑ ይህን ለማስወገድ እንዲቻል የተሻሻለው አዋጅ በፌዴራልም ሆነ በክልል ለሚታዩ የሙስና ወንጀሎች ተፈፃሚ በሚሆን መልኩ እንዲቀረጽ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተሻረው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ላይ የማይታገዱ ንብረቶች ዝርዝር የተመለከተ ቢሆንም ዝርዝሮቹ በበቂ ሁኔታ ያልተጠቀሱ በመሆኑ በተሻሻለው አዋጅ አንቀጽ 10 ላይ ተሟልተው ቀርበዋል፡፡

በሌላ በኩል በተሻረው አዋጅ አንቀጽ 38 «ዝምታ እንደማመን ይቆጠራል» በሚል የተቀመጠው አገላለጽ የተከሳሽን በራሱ ላይ እንዲመሰክር ያለመገደድ ህገ መንግሥታዊ መብት እንደሚያጣብብ ስለታመነበት በተሻሻለው አዋጅ ላይ እንዳይካተት ተደርጓል፡፡

ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው የማሻሻያ አንቀጽ በተሻረው አዋጅ ላይ በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው የዋስትና መብት እንደሌለው የሚደነግገው ነው፡፡ የዋስትና መብትን በአጠቃላይ መከልከሉ ደግሞ በሙስና ወንጀል ምርመራ ስራ ላይ እንቅፋት ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ይኸውም በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው የዋስትና መብት የሌለው በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ለመፈጸሙ ጥቆማ ሲደርሰው በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ ሳይኖረው ተጠርጣሪውን ቢይዘው እንደማይለቀቅ ስለሚያውቅ ከመያዙ በፊት የተሟላ መረጃ ይፈልግ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የምርመራ ስራውን በጣም አስቸጋሪ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡

ለምሳሌ የዋስትና መብት መከልከል መርማሪው ለመክሰስ የሚያበቃው መረጃ ሳይገኝ ተጠርጣሪን ከመያዝ እንዲቆጠብ ስለሚያደርገው በምርመራ ሂደት ተከሳሹን በመያዝ ከተከሳሹ ሊያገኘው ይችል የነበረውን የእውነት ቃል የማግኘት ዕድሉን ያሰናክለዋል፡፡ በሌላ በኩል የተሟላ ማስረጃ ባልተደራጀበት ሁኔታ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ቃል ለመቀበል መሞከር ደግሞ ባልተሟላ ማስረጃ ተጠርጣሪ ተይዞ የሚጉላላበት ሁኔታ ያስከትል ነበር፡፡ ተጠርጣሪው ባልተያዘበት ሁኔታ ደግሞ ምስክሮችን ጠርቶ ቃል ለመቀበል መሞከር ተጠርጣሪው ስለሁኔታው መረጃ ሊደርሰው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ስለሚሆን ማስረጃዎችን ለማጥፋት ሊንቀሳቀስ የሚችልበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩት በአብዛኛው የመንግሥት ሠራተኞች ወይም ባለሥልጣናት ስለሚሆኑ ተጠርጣሪው ሳይያዝ፣ እንዲሁም በእሱ ላይ ምርመራ መጀመሩን እንዳያውቅ በማድረግ ማስረጃ ማሰባሰብ በጣም ያስቸግራል፡፡ ይህም የምርመራ ስራውን ምን ያህል ሲጐዳው እንደቆየ መገመት ይቻላል፡፡

በመሆኑም በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ መሠረት አንድ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው ከአስር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል የሙስና ወንጀል የተከሰሰ ካልሆነ፣ ወይም ተጠርጣሪው በዋስትና ቢለቀቅ ያመልጣል፣ ማስረጃ ያጠፋል ወይም ሌላ ወንጀል ይፈጽማል ተብሎ ካልተገመተ የዋስትና መብቱን ሊያስከለክለው አይችልም፡፡

ቀጠይ ሁለት