News
The profile of the FEAC
Major objectives of FEAC
Amendment of the Proclamation
The revised establishment proclamation
The revised procedural proclamation
Directives and regulations
Principles and values
Annual Report
Publications
Vacancies
Contact Us
 proclamation pdf

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምሥረታ እና እንቅስቃሴዎቹ

 

5   የኮሚሽኑ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማዎች፣ ስትራቴጂክ ዕቅድ  ሥልጣንና ተግባር፣ እንዲሁም መርሆዎችና እሴቶች

5.1     የኮሚሽኑ ራዕይ

5.2      የኮሚሽኑ ተልዕኮ

5.3    ኮሚሽኑ ዓላማዎች

5.4    ስትራቴጂክ ዕቅድ

5.5     የኮሚሽኑ ዋና ዋና ስልጣንና ተግባራት

5.6    የኮሚሽኑ መርሆዎችና እሴቶች

5.6.1 የኮሚሽኑ መርሆዎች

5.6.2 የኮሚሽኑ እሴቶች

6. የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መዋቅር

6.1 የሥነ ምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

6.2 የሙስና መከላከል መምሪያ

6.3 የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ

6.4 ዐቃቤ ሕግ መምሪያ

6.5  የአስተዳደር መምሪያ

6.6 የውስጥ ኦዲት፣ የፕላንና ፕሮግራም እንዲሁም የሕግ አገልግሎቶች

6.7 የክልል ግንኙነት ጉዳይ ጽ/ቤት 

ቀጣይ ሦስት

 

5.  የኮሚሽኑ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማዎች፣ ስትራቴጂክ ዕቅድ  ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም መርሆዎችና እሴቶች

5.1 የኮሚሽኑ ራዕይ

በመልካም ሥነምግባር የታነፀና ሙስናን አምርሮ የሚታገል ህብረተሰብ ተፈጥሮ ሙስና የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ደርሶ ማየት፣

5.2  የኮሚሽኑ ተልዕኮ

የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርትን በማስፋፋት በፌዴራል የመንግሥት /ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የአሠራር ሥርዓትን በማጥናትና እንዲሻሻሉ በማድረግ በፌዴራል መንግሥትና ከፌደራል መንግሥት ለክልሎች ከሚሰጡ ድጐማዎች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ፣ በመመርመርና በመክሰስ የሀገሪቱ ሀብት ለልማት እንዲውል ማድረግ፤

5.3 ኮሚሽኑ ዓላማዎች

·        አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት የነቃ እና ሙስናን ሊሸከም የማይችል ሕብረተሰብ እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ፣

·        አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሠራርን መከላከል፣

·        የሙስና ወንጀልን እና ብልሹ አሠራርን ማጋለጥ፣ መመርመር እና መክሰስ ናቸው፡፡ 

5.4  ስትራቴጂክ ዕቅድ

ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በተዘጋጀው የኮሚሸኑ የአራት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ የሚከተሉት ስድስት ስትራቴጂክ ጉዳዮች በዐበይትነት የተካተቱ ሲሆኑ እነዚህም የማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራትን መለየት፣ የተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን መዘርጋት፣ በሥራ ሂደት ላይ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመሥረት፣ የተቀላጠፈ የኢንፎርሜሽን ሥርዓት መዘርጋት እና ኤች.አይ.ቪ./ኤድስን በመከላከል ተግባር ላይ መሳተፍ ናቸው፡፡ በስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ የኮሚሽኑ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ መርሆዎች፣ እሴቶች፣ ዓላማና ግቦች በዝርዝር ተመልክተዋል፡፡

5.5 የኮሚሽኑ ዋና ዋና ስልጣንና ተግባራት

ኮሚሽኑ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት አሉት

  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ስለሙስና ጐጂነት የህዝቡ ንቃተ ህሊና እንዲጐለብት በማስተማር እና መልካም ሥነምግባር በሕዝብ አገልግሎት እና በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲስፋፋ በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መዋጋት፣
  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በመንግሥት መ/ቤቶች እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡና ሊጋለጡ የሚችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን በማጥናት ወይም እንዲጠኑ በማድረግ እንዲሻሻሉ ማማከርና ማሳሰብ፣ የአሠራር ስርዓቶቹ የተሻሻሉ መሆናቸውን መከታተል እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ተገቢ የሆነው እርምጃ እንዲወሰድ ወይም ውሣኔ እንዲሰጥ አግባብ ላለው አካል በማሳወቅ ወይም በማሳሰብ ሙስናን የመከላከል፣ በሌሎች ሰዎች ሲጠየቅ ተመሳሳይ ምክርና ድጋፍ የመስጠት፣
  • በመንግሥት መ/ቤቶች እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከባድ የሥነምግባር መጣስ ስለመፈፀሙ ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው የማጣራት ወይም እንዲጣራ የማድረግ እና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ የመከታተል፣
  • በመንግሥት መ/ቤቶች ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም ፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች ከሚሰጠው ድጐማ ጋር በተያያዘ በክልል መ/ቤቶች በወንጀል ህግ እና በሌሎች ሕጐች ውስጥ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች በመንግሥት ሠራተኞች ወይም ባለሥልጣኖች ወይም በሌሎች ­ዎች ስለመፈፀማቸው ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው የመመርመርና የመክሰስ ወይም እንዲመረመር ወይም እንዲከሰስ የማድረግ፣
  • ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው በማናቸውም ባንክ የሚገኝ የተጠርጣሪ­ዎች የባንክ ሂሳብ በኮሚሽነሩ ትዕዛዝ እንዲመረመር የማድረግ፣ መረጃ የማግኘት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲከበር የማድረግ፣
  • ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በምርመራ ላይ ያሉ ­ዎች ሀብት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ፣ በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ የተረጋገጠን ወይም በሙስና ወንጀሉ ከተገኘው ጥቅም ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ማናቸውም ንብረት ወይም ሀብት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲወረስና በሐራጅ ተሸጦ ወይም ሳይሸጥ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን የማድረግ፣
  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በህግ በሚደነገገው መሠረት የመንግሥት ባለሥልጣኖችን እና በህግ ሀብታቸውንና የገንዘብ ጥቅማቸውን እንዲያስመዘግቡ ግዴታ ያለባቸውን የመንግሥት ሠራተኞች ሀብትና የገንዘብ ጥቅሞች መዝግቦ የመያዝ ወይም ተመዝግበው እንዲያዙ የማድረግ፣
  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር ለሙስና ወንጀል ጠቋሚ­ችና ምስክሮች የአካልና የሥራ ዋስትና ጥበቃ የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በህግ በሚወሰን መሠረት ጥበቃ የመስጠት፣
  • ሕግ አውጪና የዳኝነት አካላትን ሳይጨምር ለመንግሥት መ/ቤቶችና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚያገለግሉ የሥነምግባር ደንቦች መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ ወይም ማዘጋጀት እና አፈፃፀማቸውን የመከታተል፣ ከሕግ አውጭ እና ከዳኝነት አካላት ጥያቄ ሲቀርብለት በሥነምግባር ደንብ አዘገጃጀት ረገድ ምክር የመስጠት፣
  • አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሥነምግባር አውታሮችን የማስተባበር፣
  • በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ የሥነምግባር መከታተያ ክፍሎች እንዲቋቋሙ ድጋፍ የማድረግ፣
ለክልሎች አስፈላጊውን የምክርና የድጋፍ አገልግሎት የመስጠት ናቸው፡፡

5.6 የኮሚሽኑ መርሆዎችና እሴቶች

5.6.1 የኮሚሽኑ መርሆዎች

ኮሚሽኑ የሚከተሉት መርሆዎች አሉት፡-

1.      ቅንነት             7. ለሕዝብ ጥቅም መሥራት

2.      ታማኝነት           8. ሥልጣንን በአግባቡ መጠቀም

3.      ግልፅነት            9. ከአድልዎ ነፃ መሆን

4.      ምስጢር መጠበቅ    1ዐ. ህግን ማክበር

5.      ሐቀኝነት           11. ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ

                                                መስጠት

6.      ተጠያቂነት         12. አርአያ መሆን

5.6.2 የኮሚሽኑ እሴቶች

1.      የመልካም ሥነምግባር ተምሳሌት ነን

2.      ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነትና የዓላማ ጽናት መለያዎቻችን ናቸው

3.      የፀረ-ሙስና ትግል አጋራችን ሕብረተሰባችን

4.      በመልካም ሥነምግባር የታነፀ ዜጋ ማፍራት ግንባር ቀደም ዓላማችን ነው

5.    ሙስናን መዋጋት ልማታችንን ማፋጠን ነው፣ የሚሉ ናቸው፡፡

6. የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መዋቅር

 

ኮሚሽኑ አምስት መምሪያዎችን፣ ሦስት አገልግሎቶችን እና ሦስት /ቤቶችን በውስጡ አካትቷል፡፡ መምሪያዎቹ የሥነምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት፣ የሙስና መከላከልና ምርምር፣ የምርመራ፣ የፀረ-ሙስና ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም የአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያዎች ናቸው፡፡ በአገልግሎት ደረጃ የተደራጁት ደግሞ የሕግ፣ የኦዲት እና የኘላንና ኘሮግራም አገልግሎቶች ሲሆኑ በጽሕፈት ቤት ደረጃ የተዋቀሩት ደግሞ የኮሚሽነር /ቤት የምክትል ኮሚሽነር /ቤት እና የክልል ግንኙነት /ቤት ናቸው፡፡ ለሙሉ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ከዚህ ቀጥሎ የእያንዳንዳቸው ተግባራት ዘርዘር ብለው ቀርበዋል፡፡

6.1 የሥነ ምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

 

የሥነምግባር ትምህርት እና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ተጠሪነቱ ለም/ኮሚሽነር ሲሆን፣ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሥነ ምግባር ትምህርትን በማስፋፋትና በማስረጽ እንዲሁም የኮሚሽኑን ራዕይ፣ ተልዕኮና እንቅስቃሴ በማሳወቅ ሙስናን የማይሸከም ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በዋነኝነት ለማሳካት የተደራጀ ነው፡፡

 

መምሪያው በዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን የሥነምግባር ትምህርት እና የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥኖችን በመያዝ የተደራጀ ነው፡፡ እነዚህም ዲቪዥኖች በምክትል ዳይሬክተር ይመራሉ፡፡ እያንዳንዱ ዲቪዥን ደግሞ በሁለት ቡድኖች ይከፋፈላል፡፡ በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርት ዲቪዥን በስሩ የመደበኛ ትምህርት ተቋማት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን፣ የመንግሥት መ/ቤቶችና የሲቪል ማህበራት የሥነምግባር ትምህርትና ሥልጠና ቡድንን ሲያጠቃልል፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ደግሞ በበኩሉ የመገናኛ ብዙኃን ዝግጅት ቡድንን እና የሕዝብ ግንኙነት ቡድንን ያቅፋል፡፡ 

በዚህ መሠረት የመምሪያው የሥራ እንቅስቃሴ የሚመራው በአንድ ዳይሬክተር፣ በሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች እና በአራት የቡድን ኃላፊዎች ሆኖ በአጠቃላይ በ33 የሰው ኃይል የተደራጀ ነው፡፡

በመምሪያው ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በዲኘሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው፡፡ የሙያ ስብጥራቸውም ቋንቋና ሥነጽሁፍን፣ ትምህርትን፣ ፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነትን፣ ትያትር ጥበባትን፣ ሥርዓተ ትምህርትን፣ ኮሙኒኬሽንን እና ሳይኮሎጂን ያጠቃልላል፡፡ ባለሙያዎቹም በአብዛኛው በማስተማር፣ በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ በጋዜጠኝነት፣ በአሰልጣኝነት ወዘተ.. የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡

ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ እንደማይችል ሙስናን ለመከላከል የተደረጉ የሌሎች ሀገሮች ጥረቶች ተሞክሮ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በሙስና ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ከሚደረገው የምርመራ እና የክስ ሂደት ጐን ለጐን ሙስና እና ብልሹ አሠራር በአንድ አገር ላይ ስለሚያደርሱት የከፋ ጉዳት ሕብረተሰቡን በስፋት ማስተማር አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ሙስናን የመዋጋቱ ተግባር በአንድ ተቋም ብቻ እየተከናወነ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ሙስናን የማይሸከም ሕብረተሰብ በመፍጠር በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ የሁሉንም ሕብረተሰብ ተሳትፎ ማግኘት የግድ ነው፡፡

በዚህ መሠረት የሥነምግባር ትምህርትና ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ከተለያዩ ተቋማትና የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር በመልካም ሥነምግባርና በፀረ-ሙስና ዙሪያ የተለያዩ የማስተማር ዘዴዎችን በመጠቀም ትምህርት ይሰጣል፡፡ መምሪያው ከሚከተላቸው የማስተማር ዘዴዎች መካከል፡-

  • መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣
  • የኮሚሽኑን የኘሬስ ውጤቶች በማዘጋጀት፣
  • በግንባር -face to face- በመገናኘት እና
  • ቅንጅት በመፍጠር
የሚያከናውናቸው ትምህርታዊ አቀራረቦች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

6.2 የሙስና መከላከል መምሪያ

የሙስና መከላከልና ምርምር መምሪያ ተጠሪነቱ ለም/ኮሚሽነር ሲሆን፣ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ከኮሚሽኑ ዓላማ አስፈፃሚ መምሪያዎች አንዱ ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡

መምሪያው የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ይችል ዘንድ 28 ባለሙያዎችንና የሥራ ኃላፊዎችን በመያዝ በሦስት ዲቪዥኖች ተደራጅቶ ይገኛል፡፡ ዲቪዥኖቹም፡-

·        የሙስና መከላከልና ምርምር ዲቪዥን -ዲቪዥን አንድ-

·        የሙስና መከላከልና ምርምር ዲቪዥን -ዲቪዥን ሁለት-

·        የሥነምግባር ምርምር ማዕከል -ዲቪዥን ሦስት- ሲሆኑ፣ በሰው ኃይል በኩል ከላይ ከተጠቀሱት ውስጥ አንድ የመምሪያ ዳይሬክተር፣ ሦስት ምክትል ዳይሬክተሮችና ሁለት ፀሐፊዎች ይገኙባቸዋል፡፡

·        መምሪያው በአዋጅ ቁጥር 433/97 ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከመከላከል ጋር የተያያዙት  ሥልጣንና ተግባራት በቀጥታ ይመለከቱታል፡፡ እነዚህም ሥልጣንና ተግባራት ጠቅለል ብለው ሲታዩ-

·        የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችን ማካሄድ፣እንዲሁም

·        የምርመራ ሥራና የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ የማዘጋጀት ተግባራትን የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡

መምሪያው  እስካሁን ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት-

መምሪያው ከላይ የተገለፀውን አደረጃጀትና የሰው ኃይል በመያዝ የሚከተሉትን ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የአሠራር ሥርዓት ጥናቶችና የምርምር ሥራ

የሙስና መከላከልና ምርምር መምሪያ የመንግሥት መ/ቤቶችንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማዕከል በማድረግ የአሠራር ሥርዓት ጥናቶች ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን መምሪያው ከሙስና እና ከሥነምግባር ጋር የተያያዙ የምርምር ጥናቶችንም ያካሂዳል፡፡

የምርምር ሥራ፣ የማስፈፀሚያ ደንብና መመሪያ ዝግጅት

ከሙስና እና ከሥነምግባር ጋር የተያያዙ የምርምር ጥናቶችን ማካሄድና የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ ሕግ ለማስፈፀም የሚያግዙ ደንቦችና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ለሚመለከታቸው አካላት አስቀርቦ እንዲፀድቅ ክትትል የማድረግ ሥራዎችን ማከናወን ከመምሪያው የሚጠበቅ ሁለተኛው ዐቢይ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡

መምሪያው የአሠራር ሥርዓት ጥናት እና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን የሚከተላቸው ስልቶች

በመንግሥት መ/ቤቶች እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር የተጋለጡና መጋለጥ የሚችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን በማጥናት እንዲሻሻሉ የማማከርና የማሳሰብ አገልግሎቶችን ቁጥራቸው ከ360 ለሚበልጡ የመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች በአንድ ጊዜ ለማከናወን ኮሚሽኑ አሁን ባለው ውስን የሰው ኃይልና አደረጃጀት አዳጋች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የግዴታ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚጠኑ ተቋማትን መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡

በመሆኑም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት ተቋማትን የአሠራር ሥርዓት ጥናት ለማካሄድ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚጠኑ መንግሥታዊ ተቋማትን ለመምረጥ የሚያስችሉ መስፈርቶች የያዘ የመምረጫ መመሪያ በኮሚሽኑ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል፡፡

ከሕዳር 1997 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር ከተጋለጡ የመንግሥት መ/ቤቶችና የልማት ድርጅቶች መካከል ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የአሠራር ሥርዓት ጥናት የሚካሄድባቸውን ተቋማት ለመለየትና ደረጃ ለማውጣት የሚያስችል መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል፡፡

መምሪያው የአሠራር ሥርዓቶቻቸው የሚጠኑ ተቋማትን ለመምረጥ ከሚጠቀምበት መመሪያ በተጨማሪ የተመረጡት ተቋማት የአሠራር ሥርዓት ምን ላይ ተጀምሮ የት መጠናቀቅ እንዳለበት የሚያመላክት የአሠራር ሥርዓት የአፈፃፀም መመሪያ አዘጋጅቶ ተፈፃሚ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ይህን የአሠራር ሥርዓት ጥናት መመሪያ ተከትሎ ሥራን ለማቀላጠፍና የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማትን የአፈፃፀም ብቃትና የአሠራር ሥርዓቶች በተፋጠነ ሁኔታ ለማጥናት የሚያስችለው አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡ 

የተሻሻለው ይህ የአሠራር ሥርዓት ጥናት መመሪያ የድህረ አሠራር ሥርዓት ጥናት አፈፃፀም ክትትል ሥራ የት ተጀምሮ እንዴት ተከናውኖ በምን ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚያመላክት አሠራርን በዝርዝር ያመለክታል፡፡

6.3 የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ

 

መምሪያው ተጠሪነቱ ለኮሚሽነሩ ሲሆን፣ በመንግሥት /ቤቶች ወይም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወይም የፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች ከሚሰጠው ድጐማ ጋር በተያያዘ በክልል መ/ቤቶች በወንጀል ሕግ እና በሌሎች ሕጐች ውስጥ የተመለከቱት የሙስና ወንጀሎች በመንግሥት ሠራተኞች ወይም ባለሥልጣኖች ወይም በሌሎች ሰዎች ስለመፈፀማቸው ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው የመመርመር  ወይም እንዲመረመር የማድረግ ተግባርና ኃላፊነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር የመምሪያው ዋና ተግባር የተጠረጠሩ የሙስና ወንጀሎችን እና የሥነምግባር ጥሰቶችን በማጣራት ጥፋተኞች ክስ እንዲመሰረትባቸው የምርመራውን ውጤት ለዐቃቤ ሕግ መምሪያ ማስተላለፍ ነው፡፡

ሰላሣ ስምንት ባለሙያዎች ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 5 የፀጥታ ሠራተኞች ያሉት ይህ መምሪያ ከተለያዩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች የሚደርሱትንና በሙስና ወንጀል እና በሥነምግባር መተላለፍ ዙሪያ የሚያተኩሩ ጥቆማዎችን በአካል፣ በስልክ፣ በደብዳቤ፣ በፋክስ እና በኢሜል አማካኝነት በመቀበል እንደችግሩ ይዘትና ስፋት ጥቆማው በቅደም ተከተል የሚደራጅበትንና ለምርመራ ዝግጁ የሚሆንበትን አሠራር ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መምሪያው የተጠርጣሪዎች ሀብት በፍርድ ቤት አማካኝነት እንዳይንቀሳቀስ በማስወሰን ተጠራጣሪዎቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ ፍርድ ቤት በሚወስነው መሠረት የታገደው ንብረት ለፍርድ ማስፈፀሚያ እንዲውል ሊያደርግ ይችላል፡፡

ከሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ ባለሙያዎች መካከል አንድን የተጠረጠረ የሙስና ወንጀል ጉዳይ እንዲመረምር የተመደበ ሠራተኛ ለምርመራ ሂደቱ ጠቃሚነት አለው ተብሎ እስከታመነበት ድረስ ከማንኛውም ድርጅት ወይም ግለሰብ መረጃ የማግኘት መብት አለው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ምርመራቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪ የሙስና ወንጀሎችን ጉዳይ በተመለከተ መረጃ እንዲሰጥ የሚጠየቅ ማንኛውም አካል በተጠየቀው ጉዳይ ላይ መረጃ ለመስጠት ትብብር ሊያሳይ የሚገባው መሆኑን ነው፡፡

የሙስና ወንጀል ምርመራ መምሪያ ዳይሬክተር በሙስና የተጠረጠረን ግለሰብ ወይም ጉዳዩ በምርመራ ላይ የሚገኝን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንዲውል የሚያስገድድ አሳማኝ ምክንያት ካለው ከ48 ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ በቁጥጥር ስር እንዲውል ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን አለው፡፡ ይህም ሲሆን ጉዳዩን በቅድሚያ ለሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አሳውቆ ስምምነት ማግኘት ይኖርበታል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ማንኛውም የመንግሥት ተቋምም ሆነ ግለሰብ ከባድ የሥነምግባር መጣስን ጨምሮ  የሙስና ወንጀል ለመፈፀሙ ጥርጣሬ ሲኖረው ጉዳዩን ለኮሚሽኑ እንዲጠቁም ይጠበቃል፡፡

የተወሰኑ የመምሪያው ተግባራት እንዳስፈላጊነቱ በሚስጥር የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ መንግሥታዊ ተቋም የሙስና ወንጀል ለመፈፀሙ ጥቆማ ለማቅረብ ወደ ኮሚሽኑ የሚመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ማንነት በሚስጥር ሊጠበቅላቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም በጅምር የምርመራ ደረጃ ላይ ለሚገኝ ጉዳይ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ፍንጫቸው እንዳይጠፋና ተፈላጊ መረጃዎቹም እንዳይሰወሩ ለማድረግ በሚስጥር ተጠብቆ መቆየቱ ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን የሙስና ወንጀልን የማጣራት ሂደት በሚስጢር ተጠብቆ የሚቆየው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ብቻ ነው፡፡

መምሪያው በጥቆማ የሚቀርቡለትን የተጠረጠሩ የሙስና ወንጀሎች ጉዳይ አንዱን ከሌላው ሳያበላልጥ ለሁሉም እኩል ትኩረት ሰጥቶ የምርመራ ሥራውን ያካሂዳል ምክንያቱም በጥቆማ አቀራረብ ላይ ዝቅተኛ የሙስና ወንጀሎች መስለው የሚታዩ ጉዳዮች በምርመራ ሂደት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ያካተቱ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሌላ ወገን ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል በፀረ-ሙስና ዘመቻው ላይ የሚያሳየው ተሳትፎ የተጠናከረ እንዲሆን ከተፈለገ ሁሉም ዜጋ ለኮሚሽኑ በጥቆማ የሚያቀርባቸው የሙስና ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው መጣራት ስለሚገባቸው ነው፡፡

ይህም በአነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሙስና ወንጀሎች ሳይቀሩ በኮሚሽኑ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተገቢው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉ ሙስናን ሊሸከም የማይችል  ሕብረተሰብ  ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦ ስለሚኖረው የትኛውም የሙስና ወንጀል ከሕዝብ ዕይታ ተሰውሮ ብዙ እንዳይቆይ ያደርጋል፡፡

6.4 ዐቃቤ ሕግ መምሪያ

 

የፀረ-ሙስና ዐቃቤ ሕግ መምሪያ ተጠሪነቱ ለኮሚሽነሩ ሲሆን በፌደራል ሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥር ከተደራጁት ዓላማ አስፈፃሚ መምሪያዎች አንዱ ነው፡፡ መምሪያው የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው በቂ ባለሙያዎች እንዲኖሩት በመዋቅር ደረጃ የተመለከተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ 24 ሠራተኞችን ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የዐቃቢያነ-ሕጐች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የሙያተኞች እጥረት የሚታይበት ነው፡፡

መምሪያው የተደራጀበት ዋና ዓላማ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ የተጣራባቸውን ፋይሎች መርምሮ ወንጀል ፈፃሚ ተጠርጣሪዎችን ስልጣን ባለው ፍ/ቤት ክስ መስርቶ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ እና በሙስና ወንጀል የተገኘን ንብረት በማሳገድ እና እንዲወረስ በማድረግ በፀረ-ሙስና ትግሉ ጉልህ የሙስና ወንጀል የመከላከል ተግባርን ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡

·        ይህን ዓላማ ተፈፃሚ ለማድረግ መምሪያው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹ-

·        በወንጀል ሕግ እና በሌሎች ሕጐች የሙስና ወንጀሎች ፈፅመዋል ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ምርመራ የተጣራባቸው የምርመራ መዛግብት ሲደርሱት በማጥናትና በመመርመር በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸውን ክስ ሊቀርብባቸው አይገባም የሚል ውሣኔ በመስጠት ይዘጋል፣ ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልጋቸውን የምርመራ መዝገቦች ተጨማሪ ምርመራ ተደርጐ ምርመራው ተጠናክሮ ውጤቱ እንዲቀርብለት ለመርማሪው አካል ይመልሳል፣ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ በተሰባሰበባቸው የሙስና ወንጀል ምርመራ መዝገቦች ላይ በፍ/ቤት የወንጀል ክስ መስርቶ ተገቢውን በመፈፀም የመፋረድ፣

·        በሙስና ወንጀል ድርጊት ከተገኘ ንብረት ጋር በተያያዘ በምርመራ ላይ ያሉ ሰዎች ሀብት በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ የማሳገድ፣

·        በሙስና ወንጀል የተገኘ ለመሆኑ የተረጋገጠን ማንኛውንም ንብረት ወይም ሀብት በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲወረስና በሀራጅ ተሸጦ ወይም ሳይሸጥ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን የማድረግና

·        ስለመመርመርና ስለመክሰስ በወንጀል ሕግ ሥነሥርዓትና በሌሎች ሕጐች ለዐቃቤ ሕግ በተሰጠ ሥልጣን መሠረት ኮሚሽኑን በሚመለከቱ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ላይ ተገቢውን የመፈፀም ተግባራትን ያከናውናል፡፡

 የፀረ-ሙስና  ዐቃቤ  ሕግ መምሪያ ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት

·        ከኮሚሽኑ ምርመራ መምሪያ እና ከሌሎች የምርመራ አካላት ጋር

የዐቃቤ ሕግ መምሪያ ግንኙነቱ በግንባር ቀደምትነት የተመሠረተው በኮሚሽኑ ሥር ከተደራጀው የምርመራ መምሪያ ጋር ሲሆን ይህ መምሪያ ከዐቃቤ ሕግ መምሪያ ጋር ያለው ግንኙነት የተመሠረተው ራሱ ባሉት መርማሪዎች አማካኝነት በሚያከናውናቸው የምርመራ ተግባራት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ማለትም ከፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መምሪያ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ መምሪያ እና ከክልል መንግሥታት ፖሊስ የምርመራ መምሪያዎች ተጠናቀው በሚደረሱት የምርመራ መዛግብትም ጭምር ነው፡፡ ምርመራቸው የተጠናቀቁ ሁሉም መዛግብት ለዐቃቤ ሕግ መምሪያ የሚደርሱት በኮሚሽኑ ምርመራ መምሪያ በኩል በመሆኑ ሁለቱ የኮሚሽኑ መምሪያዎች የጠበቀ የዕለት ተዕለት የሥራ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎችን በመያዝ፣ ለምስክሮች መጥሪያ በማድረስ እንዲሁም የሚታገዱ ንብረቶችን በማጥናት በኩል የሚደረገው የሥራ ግንኙነት ሁለቱን በጋራ የሚያገናኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡

·        ከፍርድ ቤቶች ጋር

የፀረ-ሙስና አቃቤ ሕግ መምሪያ ከምርመራ መምሪያ ቀጥሎ ከፌደራል ፍርድ ቤቶች እና ከክልል  ጠቅላይ  ፍርድ ቤቶች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው፡፡ የግንኙነቱም መሠረት መምሪያው በፍርድ ቤቶች የሚያስከፍታቸው የሙስና ወንጀል ክስ ፋይሎች ሲሆኑ ትክክለኛ ፍትህ ሳይዘገይ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻች በጋራ ይሰራሉ፡፡

·        ከሌሎች የዐቃቤ ሕግ ተቋማት ጋር

የፀረ-ሙስና ዐቃቤ ሕግ መምሪያ በፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሥር ከተደራጀበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ከሌሎች የዐቃቤ ሕግ ተቋማት ጋር የተመሠረተ ቀጥተኛ የሆነ የሥራ ግንኙነት ባይኖርም አልፎ አልፎ ከኮሚሽኑ ሥልጣን ክልል ውጭ የሆኑ የምርመራ መዛግብት ሲያጋጥሙ በመሸኛ መረጃ የሚለዋወጡበት አሠራር የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ወደፊት የተሻሻለውን የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 መሠረት በማድረግ የፌዴራሉም ሆነ የክልል ዐቃቤ ሕግ ተቋማት እና የክልል ሥነምግባር እና  የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤያነ-ሕግ የፌዴራሉን መንግሥት እንዲሁም የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ዐቃቤ ሕግ ወክለው የፌዴራሉን መንግሥት የሚመለከቱ የሙስና ወንጀሎችን ሲከሱና ሲከራከሩ በብዙ መንገድ ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚኖር ይታመናል፡፡

6.5  የአስተዳደር መምሪያ

 

መምሪያው ተጠሪነቱ ለምክትል ኮሚሽነር ሆኖ በዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን በሥሩም የፋይናንስ ዩኒትን፣ የሰው ኃይልና ስልጠና ዩኒትን፣ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒትን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዩኒትን አካቷል፡፡ መምሪያው ከዳይሬክተር በተጨማሪ አንድ ምክትል ዳይሬክተር አለው፡፡ ምክትል ዳይሬክተሩም በዋነኛነት የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒትን በበላይነት ይመራል፡፡ መምሪያው በአራቱም ዩኒቶች ወደ ሰባ ያህል የሰው ኃይል አለው፡፡

እያንዳንዱ ዩኒት በዋነኛነት የሚያከናውነውን ተግባር ለመዘርዘር ያህል የመምሪያው የፋይናንስ ዩኒት በተለይ ከፋይናንስ አስተዳደርና ከበጀት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያደራጃል በዚህ መሠረት የኮሚሽኑን የተለያዩ መሣሪያዎችና አገልግሎቶች በጀት በማዘጋጀት የኮሚሽኑን አጠቃላይ የገንዘብ አጠቃቀምና አያያዝ ይቆጣጠራል፡፡

የሰው ኃይልና ስልጠና ዩኒት የኮሚሽኑን ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ በመከተል ለኮሚሽኑ የሚያስፈልጉ ሠራተኞችን በቅጥር፣ በዝውውርና በእድገት እንዲሟሉ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ተገቢውን ሥልጠና እንዲያገኙ በየጊዜው ክትትል በማድረግ የሚያስፈፅም ሲሆን በተጨማሪም የሠራተኞችን የጡረታ፣ የሥራ መልቀቂያ፣ የፈቃድ እና ሌሎች ጉዳዮችን ያስፈፅማል፡፡

የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዩኒት ደግሞ ለኮሚሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በመግዛት ያሠራጫል፣ ያስተዳድራል፣ የጥገና ጉዳዮችንም ተከታትሎ ያስፈፅማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑን ተሽከርካሪዎች የማስተዳደር፣ የማሰማራት፣ የማስጠገን እና የዋስትና ጉዳዮችን የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ለዚህ ዩኒት ነው፡፡ የኮሚሽኑን ሕንፃ የማስተዳደር፣ ልዩ ልዩ ጥገናዎችን የማስፈፀም፣ የአገልግሎት ክፍያዎችን የመፍቀድ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን ማከናወንም የዚህ ዩኒት የሥራ ድርሻ ነው፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዩኒትም ተጠሪነቱ ለአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ ሲሆን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለኮሚሽኑ የሚያስፈልገውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚያከናውነው ይህ የሥራ ክፍል ነው፡፡

6.6 የውስጥ ኦዲት፣ የፕላንና ፕሮግራም እንዲሁም የሕግ አገልግሎቶች

 

የውስጥ ኦዲት አገልግሎት ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን አገልግሎቱ በሁለት የሰው ኃይል ማለትም በአንድ የኦዲት አገልግሎት ኃላፊ እና በአንድ ኦዲተር የተደራጀ ነው፡፡

የኦዲት አገልግሎቱ የኮሚሽኑን  የፋይናንስ መረጃዎችንና መግለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመርና የመምሪያዎችን፣ የአገልግሎቶችንና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎችን የሥራ ክንውን በመገምገም የኦዲት ሪፖርት ለማቅረብ ኃላፊነት የተሰጠው አካል ሆኖ የኦዲት ሪፖርቱንም የሚያቀርበው በቀጥታ ለኮሚሽነሩ ነው፡፡

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ዝርዝር ተግባራት መካከል፡-

  • የፋይናንስ መረጃዎችንና መገለጫዎችን ትክክለኛነት በመመርመር መረጃዎቹ የኮሚሽኑን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ማሳየት አለማሳየታቸውን በመመርመር የኦዲት አስተያየት ማቅረብ፣
  • መምሪያዎችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ያቀዱትን ሥራ ማከናወናቸውን መገምገም፣
  • በቂና አስተማማኝ የፋይናንስ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን በመገምገም የማሻሻያ ሃሳቦችን ማቅረብ፣
  • መምሪያዎች፣ አገልግሎቶችና ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ኮሚሽኑ ያለውን ሃብትና ገንዘብ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ የክዋኔ ኦዲት ማካሄድ፣
  • መሻሻል በሚገባቸው የኮሚሽኑ የገንዘብ አስተዳደር አሰራሮች ላይ የማሻሻያ አስተያየት የማቅረብ፣
  • ጥሬ ገንዘብና ሰነዶች በተለይም ቼኮች፣ የቼክ ጉራጆች፣ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኞችና ማስረጃዎች በአግባቡ መጠበቃቸውን መከታተል፣ የክፍያ ሰነዶች የሂሳብ ስሌት ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣

እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ማከናወን ለአገልግሎቱ የተሰጡ ኃላፊነቶች ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የኘላንና ኘሮግራም አገልግሎት ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን በውስጡም ከአገልግሎቱ ኃላፊ በተጨማሪ የአንድ ኤክስፐርት፣ የአንድ ስታትስቲሽያን እና የአንድ ፀሐፊ የሥራ መደቦችን እንዲያካትት ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑም ሆነ የመምሪያዎችና የአገልግሎቶች የሥራ ዕቅዶች እና መርሐ ግብሮች እንዲሁም የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዝግጅትን በማስተባበርና በማጠናቀር የተሟላ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ወቅታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ያደርጋል፣ ለውሳኔ ያቀርባል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን ያዘጋጃል እቅዶችንም ለማስፈፀም በሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የንብረት መጠን ላይ ጥናት በማድረግ ኮሚሽኑ ሊገጥመው የሚችለውን ችግር እንዴት መወጣት እንዳለበት መፍትሄ ይጠቁማል፡፡

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ሌሎች ዝርዝር ተግባራት መካከል-

  • በዕቅድና ኘሮግራም አወጣጥና፣ በሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ኮሚሽነሩን፣ /ኮሚሽነሩንና ዳይሬክተሮችን ማገዝ እና ማማከር፣
  • የኮሚሽኑን የሥራ ዕቅዶችና ሪፖርቶችን ማጠናቀር፣ ማዘጋጀት፣ ለውሳኔ አመች በሆነ መልክ ለከሚሽነሩ ማቅረብና ማማከር፣
  • የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ እንደመረጃ ማዕከል ሆኖ ማገልገል፣
  • የኮሚሽኑን መሠረታዊ መረጃዎችን ማጠናቀርና ለመረጃነት ዝግጁ ማድረግ፣
  • በኘሮጀክቶች ዝግጅት ድጋፍ ማድረግና ኘሮጀክቶችን ማዘጋጀት፣
  • የኮሚሽኑ ስትራቴጅክ እቅድ እንዲዘጋጅ ማስተባበር/ የመሪነቱን ሚና መጫወት/ እና የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄድ ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል የኮሚሽኑ ሕግ አገልግሎት ተጠሪነቱ ለኮሚሽነሩ ሲሆን አንድ የአገልግሎት ኃላፊና አንድ የሕግ አማካሪ ይዞ የተደራጀ ነው፡፡    

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል

  • ከኮሚሽኑ በሚቀርቡለት ጉዳዮች ላይ የህግ ምክር መስጠት፣
  • የህግ ሰነዶችን ማዘጋጀት እንዲሁም በሌሎች መምሪያዎችና አገልግሎቶች በሚዘጋጁ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ አስተያየት መስጠት፣ በሥራ ላይ ያሉ ደንቦችንና መመሪያዎችን  ችግር እያጠና  የማሻሻያ  ሀሳቦችን ማቅረብ፣
  • ኮሚሽኑን በሕግ ክርክር /ጉዳይ/ መወከል፣
  • በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በመመስረት ደንብና መመሪያዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም በሌሎች ተዘጋጅቶ ሲቀርብ በማዳበር ማጠናቀቅ፣
  • የቅጥርና የግዥ ውል ማዘጋጀት ይገኙበታል፡፡

ባለፉት ዓመታት አገልግሎቱ የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን በተለይም በኮሚሽኑ ተፈፃሚ ሲሆን በቆየው የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ኘሮግራም ላይ በመሳተፍና የኮሚሽኑ የተለያዩ መምሪያዎችና አገልግሎቶች ማሻሻያ ኘሮግራሙን ተፈፃሚ እንዲያደርጉ በመርዳት እገዛ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ20 በላይ የሚሆኑ መመሪያዎች ዝግጅት የተከናወነ ሲሆን ከቅሬታ ጋር በተያያዘና በሌሎችም ምክንያቶች ለቀረቡ ከ15ዐ በላይ በሆኑ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ የሕግ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎቱ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች 1ዐዐ የሚሆኑ ረቂቅ የኮንትራት ስምምነቶችን በማዘጋጀት ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር  የሕግ ውል እንዲገባ ድጋፍ አድርጓል፡፡

6.7 የክልል ግንኙነት ጉዳይ ጽ/ቤት 

የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለክልሎች አስፈላጊ የምክርና የድጋፍ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 433/97 በአንቀፅ 7-15- ላይ ተደንግጓል፡፡ ኮሚሽኑም ይህን ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልክ መወጣት ይችል ዘንድ የክልል ግንኙነት ጉዳይ /ቤትን አቋቁሟል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ተጠሪነት ለምክትል ኮሚሽነሩ ሲሆን ለክልሎች ከሚያደርገው ድጋፍ መካከል የየራሳቸው የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና አካላት እንዲያቋቁሙና በተገቢው መምራትና ማስተዳደር እንዲችሉ እንዲሁም የክልል ኮሚሽኖች በተለያየ ወቅት የሚያቀርቧቸውን የድጋፍ ወይም የትብብር ጥያቄዎችን አግባብነት በመገምገም ተገቢ መልስ እንዲያገኙ ማስቻል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑ አካላት ከክልል ኮሚሽኖች ጋር በጋራ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ተግባራትን በማቀናጀት ተግባራዊ ስለሚሆኑበት ሁኔታ ከክልል ኮሚሽኖች ጋር የመወያየትና የጋራ ዕቅድ የሚወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሌላው የጽ/ቤቱ ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል የራሳቸውን ኮሚሽን ባላቋቋሙ ክልሎች መልካም ሥነምግባርን ከማስፋፋት፣ ሙስናን ከመከላከልና የሙስና ወንጀልን ከመመርመር አንፃር ኮሚሽኑ ስለሚያደርገው ድጋፍ የማጥናት፣ የማስወሰን፣ ተግባራዊነቱን የመከታተል እና የክልል ኮሚሽን ሠራተኞች በውጭ አገር ሥልጠና ወይም ልምድ የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ተግባራትን ማከናወን ለጽ/ቤቱ የተሰጠ ሌላው ተግባር ነው፡፡

ለክልል ኮሚሽኖች ስለሚሰጥ ድጋፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ በየወቅቱ የማቅረብና ሲወሰንም ተግባራዊነቱን የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ለዚሁ ለክልል ጉዳይ /ቤት ሲሆን ለክልል ኮሚሽኖች የሚሰጠው ድጋፍ እና የሥራ ትብብርም በአብዛኛው ሥልጠና በመስጠት፣ በምክር አገልግሎት፣ በጋራ የትብብር ሥራዎች በመሳተፍ እና በአንድ ክልል የተገኘ ልምድን ወደሌላው በማስተላለፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ለክልል ኮሚሽኖች የሚሰጠው ሥልጠና ከሚያተኩርባቸው መስኮች መካከል የሙስና ወንጀል ፅንሰ-ሀሳብ ህግ፣ የሥነምግባር ትምህርትን የማስፋፋት ስልት፣ ሙስናን የመከላከል ስልት፣ የሙስና ወንጀል የምርመራ ስልት እና የሙስና ወንጀል ክስ ስልት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የምክር አገልግሎቱ የሚያተኩርባቸው መስኮችም በሙስና ምርምር እና ጥናት ዘዴ፣ በጥቆማዎች አስተዳደር፣ ኮሚሽኑን በማደራጀትና በሰው ኃይል ምልመላና አስተዳደር፤ በደንቦች፣ መመሪያዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ዝግጅት፣ በማንኛውም የፀረ-ሙስና ሕግ ጉዳይ እና የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ዘዴ ላይ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጽ/ቤቱ በጋራ የትብብር ሥራዎች ላይ የሚሳተፍባቸው መስኮች የሙስና ወንጀልን በመከላከል፣ የውይይት መድረኮችን በጋራ በማዘጋጀት እንዲሁም ሴሚናሮችን፣ ዓውደ ጥናቶችን፣ ኮንፍረንሶችን በጋራ በማዘጋጀት ዙሪያ ነው፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ጽ/ቤቱ ከክልል ኮሚሽኖች የሚያገኛቸውን ጠቃሚ ልምዶች በማሰባሰብ፣ በመተንተንና ለሌሎች የክልል ኮሚሽኖች መተላለፍ ያለበትን ለይቶ በማስወሰን ተግባራዊነቱን የመከታተል ተግባርም ያከናውናል፡፡

በአጠቃላይ የጽህፈት ቤቱን ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ ማስተባበር እንዲያስችል የኮሚሽኑ የተለያዩ አካላት በክልሎች ሊያከናውኗቸው የሚያስቧቸውን ተግባራት በዕቅድ እንዲያዙላቸው ለጽ/ቤቱ ማሳወቅ ያለባቸው ሲሆን ጽህፈት ቤቱም ዕቅድ በሚያወጣበት ወቅት የኮሚሽኑ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች በክልሎች ሊሰሩት ያሰቡት ነገር መኖር ያለመኖሩን በቅድሚያ ያረጋግጣል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ የሰው ኃይል ሊፈፀሙ ከሚችሉ ተግባራት በስተቀር ሌሎች ለክልል ኮሚሽኖች የሚሰጡ የድጋፍና የትብብር ተግባራት ሁሉ ለኮሚሽn ም/ኮሚሽነር ቀርበው ሲፀድቁ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡

ቀጣይ ሦስት