News
The profile of the FEAC
Major objectives of FEAC
Amendment of the Proclamation
The revised establishment proclamation
The revised procedural proclamation
Directives and regulations
Principles and values
Annual Report
Publications
Vacancies
Contact Us
 proclamation pdf

   10. ከባለድርሻ አካላት ጋር ስለመስራት

  11 የአገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ምስረታ

      11.1 ዳራ

      11.2 የጥምረቱ መቋቋም

  12 በወንጀል ህጉ ውስጥ የፀረ-ሙስና ህጎች ስለመካተታቸው

  13 አህጉራዊና አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ስምምነቶችን በተመለከተ

  14  ኮሚሽኑ ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሙስና ተቋማት ልምዶችን ለመቅሰም ያደረጋቸው ጥረቶ

  15 ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች

  16 በተደጋጋሚ ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

  17 ማጠቃለያ

  18  ጠቃሚ አድራሻዎች

  10. ከባለድርሻ አካላት ጋር ስለመስራት

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለጋሾች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማትና ማህበራት፣ የሐይማኖት ድርጅቶች፣ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎች፣ የክልል የፀረ-ሙስና ተቋማት፣ ፖሊስ፣ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች፣ የሰብአዊ መብትና የእንባ ጠባቂ ተቋማት፣ ዋና ኦዲተር፣ እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች በዋነኝነት ከኮሚሽኑ ጋር ሲሰሩ የቆዩ ተቋማት ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ ይብዛም ይነስም ከእያንዳንዱ ተቋም ጋር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህም እንቅስቃሴ በቀጣይ ጊዜያት እየሰፋና እየጎለበተ እንደሚሔድ ይታመናል፡፡

በተመሳሳይ የአገሪቱ የልማት አጋሮችና የውጭ መንግስታት የልምድ ልውውጥና የስልጠና ፕሮግራሞችን የደገፉበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ረገድ የሆላንድ፣ የቻይና፣ የማሌዢያ፣ የቦትስዋና፣ የደቡብ ኮሪያና የአሜሪካ መንግስታት ይጠቀሳሉ፡፡ የአለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP)፣ የእንግሊዝ የልማት ፕሮግራም ድርጅት (DFID) እንዲሁም የመንግስታቱ ድርጅት የአደንዛዥ እፅና የወንጀል መከላከል ክፍል (UNODC) የመሳሰሉት ድርጅቶች ደግሞ የኮሚሽኑን ጥረቶች በተለያዩ መንገዶች ባለፉት አስር አመታት ሲደግፉ ከቆዩ ድርጅቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የክልል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ተጠሪነታቸው ለክልል መንግስታት ነው፡፡ ከፌደራሉ የክልልና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር አቻ የሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡ የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ሙስናን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ ከነዚህ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ በስልጠናና አቅም ግንባታ ረገድ የተቻለውን ያህል ድጋፍ ሲያደርግላቸው ቆይቷል፡፡ ልምድ በመለዋወጥ ረገድም ኮሚሽኑና የክልል የፀረ-ሙስና ተቋማት ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነበራቸው፡፡ በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከሐረሪ፣ ከጋምቤላ እንዲሁም ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ጋር የነበረው ግንኙነት በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የፀረ-ሙስና ተቋም ካላቋቋሙት ከሶማሌና የአፋር ክልሎች የፍትህና የፀጥታ አካላት ጋርም ኮሚሽኑ መልካም የትብብር ስራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በመንግስት መስሪያ ቤቶችና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ከተቋቋሙ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎች ጋር የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በማስፋፋት፣ የየመስሪያ ቤቶቻቸውን የአሰራር ስርአቶች በማጥናትና የሙስና ወንጀልን በመመርመርና በመክሰስ ረገድ በትብብር ያከናወኗቸው ተግባራት በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ ለስነምግባር መኮንኖች የስልጠና፣ የምክርና የቁሳቁስ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎችን ስራ በአግባቡ ለመምራት እንዲያስችል በሚኒስትሮች ምክር ቤት አንድ ደንብ ወጥቶ ስራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ ደንቡ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የስነምግባር መከታተያ ክፍሎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ እንዲወጡ የበኩሉን አስተዋፆ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

ኮሚሽኑ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ጋር በትብብር ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በፀረ-ሙስና ትግሉ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ኮሚሽኑ የተቻለውን ሲያደርግ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በኮሚሽኑና በነዚህ አካላት መካከል የጋራ መድረኮች የተቋቋሙ ሲሆን በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ የጋራ ምክክሮች ሲካሄዱና የትግል አቅጣጫዎችንም የማመላከት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከመንግስትም ሆነ ከግሉ ሚዲያ ጋር ያለው የስራ ትብብርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሄደበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

በኮሚሽኑ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴና በአጠቃላይ በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ መገናኛ ብዙሐን ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ ኮሚሽኑ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጅ በፀረ-ሙስና ትግሉ የመገናኛ ብዙሐን ሚና ይበልጥ ማደግ እንዳለበት ኮሚሽኑ ስለሚያምን በዚህ ረገድ ጥረቱን ማጠናከር እንዳለበት ግንዛቤ ወስዶ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የመገናኛ ብዙሐን ሁለንተናዊ አቅም ሲጠናከር ለፀረ-ሙስና ትግሉ ጠቃሚ መሀኑን ለመረዳት ኮሚሽኑ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የመገናኛ ብዙሐንን አቅም ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋፆ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡

ኮሚሽኑ የሐይማኖት ድርጅቶች በፀረ-ሙስና ትግሉ ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና የጎላ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በተለይም የሐይማኖት አባቶች የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በምዕመናን ዘንድ በማስፋፋትና በማስረፅ ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይገነዘባል፡፡ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራት አባላትም አባሎቻቸውን በስነምግባር ለማነፅ የሚያደርጉት ጥረት ለኮሚሽኑ አላማዎች ስኬት የሚያበረክተው አስተዋፆ ከፍተኛ በመሆኑ ኮሚሽኑ ከነዚህ ወገኖች ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት አለው፤ ሲሰራም ቆይቷል፡፡ የሙያ ማህበራትም በፀረ-ሙስና ትግሉ የማይናቅ ድርሻ እንዳላቸው ግልፅ ነው፡፡ ማህበራቱ የየራሳቸውን የስነምግባር ደንቦች በማዘጋጀትና በአባሎቻቸው ዘንድ እንዲተገበሩ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ደግሞ ፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮንና ሌሎች ሙስናን ለመታገል የተቋቋሙ ድርጅቶችን ጥረት እንደሚያግዝ ግልፅ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ከሲቪል ማህበረሰብ፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከሐይማኖት ተቋማት፣ ከብዙሐን ማህበራትና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ሙስናን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ ተባብሮና ተቀራርቦ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የትብብር እንቅስቃሴም ወደ ፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሻል፡፡ ኮሚሽኑ በፀረ-ሙስና ትግሉ ከተለያዩ ወገኖች ጋር ያለውን ትብብርና ግንኙነት ለማጠናከር አንድ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት አቋቁሟል፡፡ ይህም የስነምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ይባላል፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ዳይሬክቶሬት ማቋቋሙ በፀረ-ሙስና ትግሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳያል፡፡

   11 የአገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ምስረታ

  11.1 ዳራ

ሙስና ከታላላቅ አለም አቀፋዊ ችግሮች አንዱ እየሆነ መምጣቱ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ በማንኛውም የአለም ክፍል እንደሚታየው በኢትዮጵያም ችግሮችን እየፈጠረ መገኘቱ ግልፅ ነው፡፡ ይህን በመረዳት የኢትዮጵያ መንግስት የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮን ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም ያቋቋመ ሲሆን ከዘጠኙ ክልሎች ደግሞ ሰባቱ የየራሳቸውን የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ተቋማት አቋቁመዋል፡፡ አገራችን በአገር ውስጥ ከምታደርገው የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃም ትግሉን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩሏን ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ከበርካታ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ተቋማት ጋርም ጤናማ የሚባል ግንኙነት ፈጥራለች፡፡ በዚህ ረገድ ከአለም ባንክና ከመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር የፈጠርነው ግንኙነት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡

በተጨማሪም አገራችን በተለያዩ ዘርፎች ሙስናን ለመታገል የተቋቋሙ የፀረ-ሙስና ኢኒሼቲቮች አባል ናት፡፡ በዚህ ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባታው ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል ሲባል የተቋቋመው Construction Sector Transparency Initiative (CoST) አባል በመሆን የነቃ ተሳትፎ ከሚያደርጉት አባላት መካከል እንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ እንዲሁም በማእድናት ዘርፍ ሙስናን ለመከላከል የተቋቋመው Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) አባል ለመሆን የሚያስችላትን እንቅስቃሴ እያደረገች ነው፡፡ የአለም አቀፍ የፀረ-ሙስና አካላት (International Association of Anti-corruption Authorities) መስራች አባልም ናት፡፡ የሐብት ማስመዝገቢያና ማሳወቂያ አዋጅ መጽደቁ፣ የወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ፣ ወዘተ በአበረታች ክንውኖች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባለፉት ዘጠኝ አመታት ሙስናን አስቀድሞ በመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝም አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ የተከናወኑት ተግባራት የሚያበረታቱና ተስፋ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ባጭሩ ባለፉት ዘጠኝ አመታት የፀረ-ሙስና ትግሉ ህዝባዊ አጀንዳ እንዲሆን ኮሚሽኑ ያደረገው ጥረት ፍሬ አፍርቷል ለማለት ያስደፍራል፡፡ 

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከሚዲያ ተቋማትና ማህበራት፣ ከሐይማኖት ድርጅቶች፣ ከብዙሐን ማህበራት፣ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት፣ በህግ ልዕልና ዙሪያ ከሚሰሩ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ሙስናን መታገልን በአላማዎቻቸው ካካተቱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከሙያ እና ብዙኃን ማህበራት ጋር የጋራ መድረኮችን አቋቁሟል፡፡ እነዚህ መድረኮች መቋቋማቸው ለፀረ-ሙስና ትግሉ ስምረት ጉልህ አስተዋፆ እንደሚያደርጉ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጅ በፀረ-ሙስና ትግሉ ከተለያዩ ወገኖች ጋር የሚደረገው ትብብር የበለጠ ይጠናከር ዘንድ የትብብር መድረኮቹ ወደ አንድ አገር አቀፍ ጥምረት መሸጋገራቸውን አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ የፀረ-ሙስና ትግሉን ስኬታማ ከማድረግ አንፃር ሁሉም ወገኖች የኛ የሚሉትና በጋራ የሚታገሉለት አንድ የጋራ ራዕይ እና አቅጣጫ መያዛቸው እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ አይነቱን የጋራ እንቅስቃሴ የሚመራ እና የሚያስተባብር አንድ አገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ማቋቋም የግድ ይላል፡፡

   11.2 የጥምረቱ መቋቋም

ኮሚሽኑ የተለያዩ ወገኖችን በማስተባበር የፀረ-ሙስና ትግሉን ወደ አንድ ምዕራፍ ለማሸጋገር ባደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሰኔ 26 ቀን 2001 ዓ.ም አንድ አገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ሊቋቋም በቅቷል፡፡ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተከናወነው ሥነሥርዓት የተቋቋመው ጥምረት የመንግስት መስሪያ ቤቶችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ የግሉን ክፍለ-ኢኮኖሚና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ ነው፡፡ የመስራች ድርጅቶቹ አወካከል እንደሚከተለው ነው፡፡

ተ.ቁ

አባል

የመቀመጫ ብዛት

ውክልና ከመቶ

ምርመራ

1

መንግስት

48

31.79%

 

2

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች

73

48.34%

 

3

የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ

27

17.88%

 

4

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች

3

1.99%

 

5

አጠቃላይ ድምር

151

100%

 

ከላይ እንደተቀመጠው መንግስት በጥምረቱ ውስጥ ያለው መቀመጫ 31.79 በመቶ ነው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከአጠቃላዩ 48.34 በመቶውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርሻ ሲጠቃለል የመቀመጫዎቹን 68.21 በመቶ እንደሚሸፍኑ እናያለን፡፡ ይህም በጥምረቱ የእለት ከለት የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ የጐላ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት እድል እንደተፈጠረላቸው አመላካች ነው፡፡ እስኪ በእያንዳንዳቸው ውስጥ ያለውን የውክልና አሰጣጥና የአባላት ዝርዝር እንደሚከተለው እንመልከት፡፡

v      የመንግስት መስሪያ ቤቶች

·         የፌደራልና የክልል መንግስታት የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች…….7x2=14

·         የራሳቸውን የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ያላቋቋሙ ሁለት ክልሎች……..5x2=10

·         ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች……………………………………………24x1=24

 

          ንዑስ ድምር=48 

v      የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች

·         ኮሚሽኑና የሙያ ማህበራት የመሰረቱት የጋራ መድረክ አባላት……22x1=22

·         ኮሚሽኑና የብዙሐን ማህበራት የመሰረቱት የጋራ መድረክ አባላት…..14x1=14

·         ኮሚሽኑ ከሚዲያ ተቋማትና ማህበራት ጋር የመሰረተው የጋራ መድረክ አባላት……25x1=25

·         ኮሚሽኑና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያቋቋሙት የጋራ መድረክ አባላት……7x1=7

·         ኮሚሽኑና የሐይማኖት ድርጅቶች ያቋቋሙት የጋራ መድረክ አባላት……5x1=5

        ንዑስ ድምር=73

v      የግሉ ሴክተር

ኮሚሽኑ ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር የመሰረተው የጋራ መድረክ አባላት….27x1=27

            ንዑስ ድምር=27 

v      ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች

በኢፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንፃራዊነት የተሻለ መቀመጫ የያዙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት………3x1=3

            ንዑስ ድምር=3

  ጠቅላላ ድምር 48+73+27+3=151

 

ከጥምረቱ ጠቀሜታዎች መካከል የሚከተሉትን በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ü      የአገር አቀፉን የፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማነትና ስኬታማነት ያሳድጋል፡፡

ü      የአገር አቀፉን የፀረ-ሙስና ትግል ተቋማዊ አሰራር ያጠናክራል፡፡

ü      የጥምረቱ አባላትም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በፀረ-ሙስና ትግሉ በንቃት የሚሳተፉበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ü      ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በስፋት የሚያሳትፈው አገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ስትራቴጂ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን፡፡

ü      የክልል መንግስታትም በዚህ ረገድ በፌደራል ደረጃ እየተካሔደ ካለው ሁኔታ በመነሳት በየክልሎቻቸው ተመሳሳይ የፀረ-ሙስና ጥምረት እንዲፈጥሩ ያነሳሳቸዋል፣ ይረዳቸዋል፡፡

እንደ ጥምረቱ አባልነቱና አስተባባሪነቱ ኮሚሽኑ በርካታ ሚናዎችን መጫወት ይጠበቅበታል፡፡ በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ እንደተመለከተው ኮሚሽኑ በጥምረቱ አባላትም ሆነ በሌሎች ባለድርሻ አካላት ሙስናን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ የሚከናወኑ ተግባራትን የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት አለበት፡፡ የጥምረቱ ቋሚ ሴክሬታሪያት የሆነው ኮሚሽኑ፣ በፀረ-ሙስና ትግሉ የጥምረቱን አባላት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱ ጥረቶችን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም በአቅም ግንባታ ረገድ የጥምረቱ አባላት አቅም እንዲጐለብት በተለያዩ መንገዶች የማገዝ ኃላፊነት አለበት፡፡ ኮሚሽኑ የጥምረቱን የስራ አፈፃፀም አጠቃላይ ሪፖርት ለጠቅላላው ጉባዔ የማቅረብ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህም በላይ የጥምረቱ አባል ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጥምረቱን እንዲቀላቀሉ የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ ይሠራል፡፡

ከሌሎች የጥምረቱ አባላት ጋር በመሆን ጥምረቱን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ረገድም ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ የጥምረቱ አባላት በውጭ አገርም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉና ሙስናን በመታገል ረገድ ልምዱ ካላቸው ድርጅቶች ልምድ የሚቀስሙበትን መንገድ የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት ኃላፊነቶች በተጨማሪ ኮሚሽኑ ጥምረቱን ለማጠናከር ይረዳሉ የሚላቸውን እንቅስቃሴዎችንም ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የክልል መንግስታትም በየክልሎቻቸው ተመሳሳይ ጥምረቶችን እንዲያቋቁሙ ያበረታታል፡፡ ሎሎች የጥምረቱ አባላትም ቢሆኑ በፀረ-ሙስና ትግሉ በንቃት በመሳተፍ፣ ጥምረቱን የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተባብሮ በመፍታትና ጥምረቱን በማጠናከር ረገድ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በእነዚህ መሰሎቹ ጥረትም ጥምረቱ የቆመለትን የፀረ-ሙስና ትግሉን በሰፊ ህዝባዊ መሠረት ላይ የመጣል ዓላማ እንደሚያሳካ ይታመናል፡፡

አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ መንግስታት፣ ኤምባሲዎች፣ አህጉራዊ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ሌሎች የጥምረቱ አባላት ያልሆኑ አጋሮች ጥምረቱን የመደገፍና የማጠናከር ኃላፊነት እንዳለባቸው እንገነዘባለን፡፡ እነዚህ ወገኖች በተለይ በአቅም ግንባታ፣ በሀሳብና በፋይናንስ ረገድ ጥምረቱን የሚያግዙበት እድል እንዳለ ይሰማናል፡፡ ይህንንም የምንለው የፀረ-ሙስና ትግሉ የማይመለከተው ወገን እንደሌለ ስለምንረዳ ነው፡፡

   12 በወንጀል ህጉ ውስጥ የፀረ-ሙስና ህጎች ስለመካተታቸው

     ቀደም ሲል በነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የፀረ-ሙስና ህጎች ለብቻቸውና ራሳቸውን ችለው የተቀመጡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ እዚህም እዛም ተበታትነው የተቀመጡበትና በተደራጀ መልኩ ራሳቸውን ችለው ያልተመለከቱበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሙስና ወንጀል ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ተቀላቅለው በተቀመጡበት ሁኔታ የትኞቹ ወንጀሎች የሙስና ወንጀሎች እንደሆኑና የትኞቹ ደግሞ ከዚህ ውጭ እንደሆኑ ለይቶ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ከሌሎች ችግሮቸ ጋር ተዳምሮ የሙስና ወንጀሎችን ለየት ባለ ሁኔታ ለመመርመር፣ ለመክሰስና ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ 

    የሙስና ወንጀሎች ከሌሎች ወንጀሎች ተለይተው አለመቀመጣቸው በህግ አስከባሪ አካላት፣ ጠበቆች፣ መርማሪዎች ዳኞች እንዲሁም በፍርድ ቤቶች አሰራሮች ላይ ክፍተቶችን በመፍጠርና አልፎአልፎም ያለመግባባት ምንጭ በመሆን ችግሮችን ሲፈጥሩ የቆዩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሙሰኞች ተገቢ ቅጣታቸውን ሳያገኙ የሚቀሩበትን ሁኔታ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ይባስ ብሎም የአንዳንዶቹን የሙስና ወንጀሎች ፈፃሚዎች ፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስቀጣት የሚያስችል ድንጋጌ ጭራሹኑ የሌለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ውስጥ እንደወንጀል አለመመልከታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ አዲሱ የወንጀል ህግ ወጥቶ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ የመጡትን ሽብርተኝነትንና አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪትን (እንደሙስና ማለታችን ነው) ወደህግ ለማቅረብ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ አልነበረም፡፡ 

    ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም በነባሩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውሥጥ የነበሩ ክፍተቶችን በመመልከት መንግስት የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን ለማሻሻል ከፍተኛ ትኩረት ሠጥቶ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም መሰረት የፀረ-ሙስና ህጎች በተሻሻለውና ግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ ውሥጥ ተለይተው፣ ተዘርዝረውና ራሳቸውን ችለው እንዲቀመጡ ሆኗል፡፡ እነዚህ ህጎች በ23 አንቀፆች የተጠቃለሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ በወንጀል ህጉ ውስጥ ተለይተውና በአንድ አካባቢ ተሰባስበው የተቀመጡ ናቸው፡፡ የእነዚህ ህጎች በተጠቀሰው መልኩ ተዘጋጅተው መቀመጣቸው ከዚህ በፊት የነበሩ የህግ ክፍተቶችን በመድፈን ሙሰኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮታል ማለት ይቻላል፡፡

    ለምስክሮች እና ጠቋሚዎች ከለላ ለመስጠት የሚያስችል የህግ ረቂቅ መዘጋጀቱ የተለያዩ የፀረ-ሙስና ህጐችን ማውጣትን በተመለከተ የሐብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ሚያዚያ 4 ቀን 2002 ዓ.ም መውጣቱ፣ የፀረ-ሙስና ልዩ የስነስርዓትና የማስረጃ ህግ ሥራ ላይ መዋሉ እንዲሁም ሙስናን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ ለሚያበረክቱ አካላትና ግለሰቦች ሽልማት ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅም ቢሆን ከነዚህ አንጻር ትልቅ ግምት የሚያሰጠው ነው፡፡ ባጠቃላይ የተጠቀሱት ህጎች በዚህ መልክ መውጣታቸው (በዝግጅት ላይ መገኘታቸው) ለፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው እሙን ነው፡፡

በወንጀል ህጉ ላይ ተለይተው የተቀመጡት የፀረ-ሙስና ህጎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

አንቀፅ 379 መንግሥታዊ ወይም ወታደራዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወይም ወደ ሐሰት መለወጥ

  1. በዚህ ምዕራፍ ከዚህ በላይ ከተመለከቱት ወንጀሎች አንዱ የተፈፀመው፡-

ሀ. በአንድ የመንግሥት መዝገብ፣ በታወቀ ሰነድ ወይም የሕዝብን ጥቅም በሚመለከት ሰነድ ላይ እንደሆነ፤ ወይም

ለ. በመንግሥት ወይም በሕዝብ መዝገብ በገባ ሰነድ ወይም ሟች እራሱ በእጁ በጻፈው ኑዛዜ ላይ እንደሆነ፤ ወይም

ሐ. የአገር መከላከያን፣ የመከላከያ ሠራዊት አቋምን፣ ድርጅትን፣ የሥራ ተግባርን ወይም ጉዳይ በሚመለከት ሰነድ ላይ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአሥራ አምስት ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እሥራት ይሆናል፡፡

2.      ወንጀሉ የተፈፀመው እነዚህን የመሳሰሉትን መዝገቦች፣ ጽሁፎች የታወቁ ሰነዶች ወይም ሌሎች ሰነዶችን እንዲያዘጋጅ፣ እንዲመዘግብ፣ እንዲጠብቅ ወይም ከነዚሁ ውስጥ ቅጅዎች እንዲሰጥ ኃላፊነት በተሰጠው የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት ይሆናል፡፡ የወንጀሉ አፈፃፀም በጣም ከባድ በሆነ ጊዜ ቅጣቱ የእድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ይሆናል፡፡

ቅንነትንና ታማኝነትን በማጓደል የመንግሥት ሠራተኞች የሚፈፅሟቸው የሙስና ወንጀሎች

አንቀፅ 4ዐ7 በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ፡-

ሀ. የተሰጠውን ሹመት ወይም ሥልጣን በግልፅ ተግባር ወይም በግድፈት ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፤

ለ. በግልፅ ከተሰጠው ሥልጣን አልፎ የሠራ እንደሆነ፤ ወይም

ሐ. ሥልጣኑ የማይፈቅድለትን ጉዳይ፣ በተለይም ሥልጣን ሳይኖረው ወይም ከሥራው ከታገደ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ፣ ወይም ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከተወ በኋላ የሠራበት እንደሆነ፤ በሕጉ ላይ ጉዳዩን በግልፅ የሚመለከት ድንጋጌ ከሌለ በቀር እንደ ነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአስር ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

  1. ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በህዝብ ወይም በመንግሥት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከሃምሳ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  2. በንዑስ አንቀፅ (2) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ፣ ቅጣቱ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከአንድ መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 4ዐ8 ጉቦ መቀበል

1.   ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ ወይም ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲሰጥ የጠየቀ፣ የተቀበለ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ፤ ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እና ከብር ሃያ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

2.      ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በህዝብ ወይም በመንግሥት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከሃምሣ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

3.      በንዑስ አንቀፅ (2) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ፣ ቅጣቱ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከአንድ መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

4.      በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (1) በተገለፀው መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ከዓለም አቀፍ የንግድ ግብይት ጋር በተያያዘ የሥራ ግዴታ ድንበር ዘለል ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ከማንኛውም የሌላ አገር መንግሥት፣ ሰው ወይም ድርጅት ጥቅም ወይም ስጦታ የጠየቀ፣ የተቀበለ፣ ለመቀበል የተስማማ እንደሆነ፣ ከዚህ በላይ ባሉት ሦስት ንዑስ አንቀጾች ስር ከተመለከቱት ቅጣቶች በአንዱ እንደነገሩ ሁኔታ ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 4ዐ9 የማይገባ ጥቅም መቀበል

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ማድረግ የሚገባውን ተግባር ለማከናወን ሲል፤ ይህንኑ ተግባር ከመፈፀሙ በፊት ወይም ከፈፀመ በኋላ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ፣ ያገኘ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር አስር ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  2. የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራትና ከብር ሰላሣ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  3. ወንጀሉ የተፈፀመው ከዓለም አቀፍ የንግድ ግብይት ጋር በተያያዘ የሥራ ኃላፊነት ወይም ግዴታ እንደሆነ፣ እንደሀገሩ ሁኔታ ከላይ በተመለከቱት ንዑስ አንቀጾች መሠረት ያስቀጣል፡፡

ንቀፅ 41ዐ አስታራቂ ሽማግሌዎችና ሌሎች ሰዎች የሚፈፅሙት የጉቦ መቀበል ወንጀል

  1. ማንኛውም አስታራቂ ሽማግሌ፣ የግልግል ዳኛ፣ የፍርድ ቤት ነባሪ፣ ንብረት ጠባቂ ወይም አጣሪ፣ ሥራውን ለማካሄድ በባለሥልጣን የተሾመ ተርጓሚ ወይም አስተርጓሚ ወይም በዳኝነት ወይም በዳኝነት ነክነት በሚታይ ጉዳይ ላይ በሙያው ረገድ አስተያየቱን ወይም የምስክርነት ቃሉን የሚሰጥ ማንኛውም ልዩ አዋቂ (ኤክስፐርት) ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ ወይም ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከተው ሰው ላይ ጥቅም ወይም ስጦታ እንዲሰጠው የጠየቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ፣ በዚህ ሕግ በአንቀፅ 4ዐ8 በመጀመሪያዎቹ ሦስት ንዑስ አንቀጾች ስር ከተመለከቱት ቅጣቶች ባንዱ እንደነገሩ ሁኔታ ይቀጣል፡፡
  2. በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (1) ከተመለከቱት ሰዎች አንዱ በተሰጠው ሥልጣን ወይም ተግባር መሠረት ማድረግ የሚገባውን ከመፈፀሙ በፊት ወይም በኋላ ጥቅም ወይም ስጦታ እንዲሰጠው የጠየቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ፤ በዚህ ሕግ በአንቀፅ 4ዐ9 በመጀመሪያዎቹ ሁለት ንዑስ አንቀፆች ላይ ከተመለከቱት ቅጣቶች በአንዱ እንደነገሩ ሁኔታ ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 411 የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፣ ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ተጠቅሞ፡-

ሀ. በንግድ ወይም በሌላ ሥራ፣ በግዥ ወይም በሽያጭ፣ ወይም ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ በማናቸውም የሥራ ግንኙነት ለግል ጥቅሙ ማናቸውንም ዓይነት ጥቅም የወሰደ ወይም ይህን ጥቅም የሚያገኝበትን ውል የተዋዋለ ወይም ሌላ ዘዴ የፈጠረ እንደሆነ፤

ለ. አግባብ ባለው ባለሥልጣን ከተወሰነው በላይ በሆነ ዋጋ የዕቃ ማቅረብ ውል፣ የሥራ መቋረጥ ውል ወይም ማናቸውንም የሥራ ውል የተዋዋለ እንደሆነ፤ ወይም

ሐ. በጠቅላላው በሥራው ሥልጣን መሠረት በአደራ የተሰጠውን ወይም ሊጠብቀውና ሊከላከለው የሚገባውን የሕዝብ ወይም የመንግሥት ጥቅም የሚጐዳ ተግባር በማናቸውም ዘዴ የፈፀመ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እና ከሃምሳ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

  1. ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በህዝብ ወይም በመንግሥት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከመቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  2. በንዑስ አንቀፅ (2) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ፣ ቅጣቱ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከሁለት መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  3. አድራጊው ጥቅም የማግኘት ወይም የማስገኘት ሀሳብ ሣይኖረው፡-

ሀ. እራሱ ወይም የቅርብ ዘመዱ ወይም ወዳጁ ባለጥቅም ወይም ባለአክሲዮን በሆነበት ድርጅት ወይም መስራች ወይም አባል በሆነበት የበጐ አድራጐት ድርጅት እና በእርሱ መሥሪያ ቤት መካከል በንግድ ወይም በሌላ ሥራ፣ በግዥ ወይም በሽያጭ፣ ወይም ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ በማናቸውም የሥራ ግንኙነት ውል እንዲፈፀም ያደረገ እንደሆነ፤ ወይም

ለ. የተወሰኑ ንብረቶችን እንዳይገዛ ወይም እንዳይጫረት በሕግ ወይም በደንብ ተከልክሎ እያለ በስሙ ወይም በሌላ ሰው ስም ወይም ከሌላ ሰው ጋር ንብረት የገዛ ወይም የተጫረተ እንደሆነ፣ በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡ ‹‹ዘመድ›› ማለት አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት ከተከሳሹ ጋር የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው ሰው ነው፡፡

አንቀፅ 412 አደራ በተሰጠው ዕቃ ያለአግባብ ማዘዝ

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሕግ አግባብ ሳይፈቀድለት፣ ሆኖም ለግል ንብረት ለማድረግ በማሰብ ሳይሆን፡-

ሀ. ታሽጐ የተረከበውን ጥቅል፣ ኢንቨሎፕ፣ ሰነድ፣ ባለዋጋ ነገሮች ወይም በአደራ ወይም እንደታሸገ የተረከበውን ማናቸውንም ዕቃ የከፈተ፣ ያስከፈተ፣ የወሰደ ወይም ያስወሰደ፣ ወይም ወሬውን የገለፀ ወይም ዕቃውን አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ፤ ወይም

ለ. እንደነዚህ ባሉ ዕቃዎች የተገለገለ ወይም ሌላ ሰው እንዲገለገልባቸው የፈቀደ እንደሆነ፤ ድርጊቱ ከባድ ቅጣት በሚወስን ሌላ ድንጋጌ የሚያስቀጣ ካልሆነ በቀር፣ ከሰባት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

  1. ወንጀሉ የተፈፀመው ጥቅም ለማግኘት በማቀድ ስሜት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እሥራትና መቀጮ ይሆናል፡፡
  2. ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኛነት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 413 በሥራ ተግባር ላይ የሚፈፀም የመውሰድና የመሰወር ወንጀል

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የማይገባ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ፡-

ሀ. በብርበራ፣ በመያዝ፣ በመውረስ ሥርዓት፣ በሀራጅ ሽያጭ፣ በሕግ ውርስ ወይም ፍርዱ በንብረት ላይ እንዲፈፀም በመወሰኑ፣ ወይም ይህን የመሰለ ማናቸውም ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ዕቃዎችን፣ ሰነዶችን፣ ባለዋጋ ነገሮችን፣ ጥሬ ገንዘቦችን፣ ተንቀሳቃሽ ወይም አላቂ ዕቃዎችን የወሰደ እንደሆነ፤ ወይም

ለ. በሥራው አጋጣሚ ምክንያት ወይም በአደራ የተረከባቸውን ወይም በእጁ ሊገቡ የቻሉትን እነዚህን የመሳሰሉትን ዕቃዎች ወይም ባለዋጋ ነገሮች የሰወረ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

  1. የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በህዝብ ወይም በመንግሥት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፤ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እሥራትና ከሠላሣ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 414 በሥልጣን መነገድ

1.      ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በሥራው ምክንያት ባለው ወይም አስመስሎ ባቀረበው ተሰሚነት፡-

ሀ. አግባብ ባለው ባለሥልጣን ተወስኖ የሚሰጥ የሥራ ደረጃ፣ ሹመት፣ ሥራ፣ ሽልማት፣ የአገልግሎት ዋጋ፣ ልዩ ችሮታ፣

ለ. በቁጥጥሩ ወይም በአሠራሩ ሥር በሚገኙ ባለሥልጣኖች ወይም የአስተዳደር ክፍሎች የሚደረግ ውል፣ የንግድ ስምምነት፣ የሥራ ጨረታ፣ የዕቃ ማቅረብ ውል፣ ወይም ሌላ ጥቅም፤ ወይም

ሐ. በአጠቃላይ ከአንድ ባለሥልጣን ወይም የአስተዳደር ክፍል የሚሰጠውን ጥቅም ወይም የሚረዳ ውሳኔ፤ ለሌላ ሰው ለማስገኘት፣ ስጦታ ወይም ሌላ ጥቅም የጠየቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና ከሠላሣ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

2.      ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የስልጣን ደረጃ ወይም በግለሰብ፣ በህዝብ ወይም በመንግሥት ጥቅም ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የወንጀሉን አፈፃፀም ከባድ አድርጐት እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከሃምሣ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

3.      በንዑስ አንቀፅ (2) ከተረዘረዘሩት ምክንያቶች ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ ተደራርበው ሲገኙ፣ ቅጣቱ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከአንድ መቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡

አንቀፅ 415 በሕገወጥ መንገድ መሰብሰብ ወይም ማስረከብ

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የማይገባውን ጥቅም ለራሱ ለማግኘት አስቦ፡-

ሀ. ሊከፈል የማይገባ መሆኑን ወይም በሕግ ከተወሰነው ታሪፍ በላይ መሆኑን እያወቀ ቀረጥ፣ ግብር፣ ልዩ ልዩ ገቢ ወይም ልዩ ልዩ የገቢ ጥቅም፣ ምንዳ፣ ደመወዝ፣ ካሣ ወይም ሌላ ወጪ የሰበሰበ ወይም እንዲሰበሰብ ያዘዘ እንደሆነ፣

ለ. ማንኛውም ዕቃ ወይም ክፍያ በሚያስረክብበት ወይም በሚሰጥበት ጊዜ ማስረከብ ወይም መክፈል ከሚገባው አሳንሶ ያስረከበ ወይም የከፈለ እንደሆነ፤ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል አሥራት፣ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና እስከ አሥራ አምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

  1. ወንጀሉ የተፈፀመው ከዚህ በላይ በአንቀፅ 414 ከተመለከቱት ሁኔታዎች በአንዱ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከሠላሣ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  2. ወንጀሉ የተደረገው በቸልተኛነት እንደሆነ፣ በቀላል እሥራትና በመቀጮ ያስቀጣል፡፡

አንቀፅ 416 ያለአግባብ ጉዳይን ማጓተት

ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራው ምክንያት በቀረበለት ጉዳይ ላይ ጥቅም ካለው ማንኛውም ሰው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ጥቅም ለማግኘት፣ በጉዳዩ ላይ ጥቅም ያለውን ማንኛውንም ወገን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት ሲል ከሕግ ወይም ከሥራ ደንብ ወይም መመሪያ ወይም ከተለመደው አሠራር ውጭ ያለ በቂ ምክንያት ያልወሰነ ወይም ያዘገየ ወይም ባለጉዳይን ያጉላላ እንደሆነ፣ በደንብ መተላለፍ ከሚያስቀጡት ሁኔታዎች ውጭ በሆነ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ በመቀጮ፣ ወይም በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 417 ዋጋ ያለውን ነገር ያለክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ ማግኘት

  1. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ተገቢ ምክንያት ሳይኖረው ያለክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ ማናቸውንም ዋጋ ያለውን ነገር የተቀበለ እንደሆነ፣ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡
  2. ንብረትን፣ የፋይናንስ አቋምን ወይም ስጦታ መቀበልን ማስመዝገብ እንደሚገባ በሕግ ወይም በደንብ በተደነገገ ጊዜ አለማሳወቅ ወይም አለማስመዝገብ በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (1)በተመለከተው መሠረት ያስቀጣል፡፡
  3. በአገሩ ወይም በአካባቢው ባህል ወይም ልማድ መሠረት እንደተራ የወዳጅነት ምልክት የሚሰጥ ዋጋ ያለው ስጦታ መቀበል ወይም ከቅርብ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ወይም ከቅርብ ወዳጅ ስጦታ ማግኘት በዚህ አንቀፅ ለተመለከተው ወንጀል ማቋቋሚያ አይሆንም፡፡

አንቀፅ 418 ያለአግባብ ፈቃድ መስጠት እና ማፅደቅ

ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ አስቦ ብቁ ላልሆነ ወይም በሕግ ሊሰጠው ለማይገባው ሰው ማናቸውንም የንግድ ወይም የሥራ ፈቃድ የሰጠ ወይም ያፀደቀ እንደሆነ ወይም አንድ ነገር የሚከናወንበትን ቦታ ያለአግባብ የፈቀደ ወይም የሰጠ እንደሆነ፣ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 419 ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ

  1. የመንግሥት ሠራተኛ የሆነ ወይም የነበረ ማንም ሰው፡-

ሀ. የኑሮ ደረጃው፣ አሁን ባለበት ወይም አስቀድሞ በነበረበት የመንግሥት ሥራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ወይም ሲያገኝ ከነበረው ሕጋዊ ገቢ የበለጠ እንደሆነ፣ ወይም

ለ. ያለው ንብረት ወይም የገንዘብ ምንጭ አሁን ባለበት ወይም አስቀድሞ በነበረበት የመንግሥት ሥራ ወይም በሌላ መንገድ ከሚያገኘው ወይም ሲያገኝ ከነበረው ሕጋዊ ገቢ ጋር የማይመጣጠን እንደሆነ፣ የዚህ ዓይነቱ የኑሮ ደረጃ እንዴት ሊኖረው እንደቻለ ወይም ያለው ንብረት ወይም የገንዘብ ምንጭ በእጁ እንዴት ሊገባ እንደቻለ ለፍርድ ቤት ካላስረዳ በቀር እንደሁኔታው የንብረቱ መወረስ ወይም ለባለቤቱ መመለስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት በመቀጮ ይቀጣል፡፡

  1. ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1(ለ) የተጠቀሰው ወንጀል በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ጊዜ አንድ ሰው ከተከሳሽ ጋር ካለው ቅርበት ወይም ሌሎች ሁኔታዎች የተነሳ ለተከሳሹ ባለአደራ በመሆን አንድን ንብረት ወይም የገንዘብ ምንጭ እንደያዘ ወይም ከተከሣሹ በስጦታ እንዳገኘ ፍርድ ቤት ካመነበት ጉዳዩን በሌላ ማስረጃ ካላፈረሰ በስተቀር ንብረቱ ወይም የገንዘብ ምንጩ በተከሣሹ ይዞታ ሥር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

ሎች ሰዎች ከመንግሥት ሥራ ጋር በተያያዘ መንገድ የሚፈጽሟቸው የሙስና ወንጀሎች

አንቀፅ 427 ጉቦ መስጠት

  1. ማንም ሰው አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ወይም ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ፣ ጥቅም ወይም ስጦታ የሰጠ ወይም ያቀረበ እንደሆነ፣ በቀላል እሥራት፣ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና ከብር አስራ አምስት ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  2. ማንም ሰው ከዓለም አቀፍ የንግድ ግብይት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለማንኛውም የሌላ አገር መንግሥት ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ወይም ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ጥቅም ወይም ስጦታ የሰጠ ወይም ያቀረበ እንደሆነ በንዑስ አንቀፅ 1 በተመለከተው መሠረት ይቀጣል፡፡
  3. ወንጀል አድራጊው ያቀረበው ጥቅም ወይም ስጦታ ከፍተኛ አንደሆነ፣ ወይም ድርጊቱ በመንግሥት፣ በሕዝብ ወይም በግለሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አሥራ አምስት ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እሥራትና ከብር ሃምሣ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  4. አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ማድረግ የሚገባውን ተግባር እንዲያከናውን ሲል፣ ይህንን ተግባሩን ከመፈፀሙ በፊት ወይም ከፈፀመ በኋላ ለዚሁ ሠራተኛ ጥቅም ወይም ስጦታ የሰጠ ወይም ያቀረበ ማንኛውም ሰው፣ እንደነገሩ ሁኔታ በመቀጮ ወይም በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
  5. ከላይ በተመለከቱት ንዑስ አንቀፆች የተገለፀው ወንጀል የተፈፀመው የሕግ ሰውነት በተሰጠው ድርጅት ከሆነ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 9ዐ(3) መሠረት በመቀጮ ይቀጣል፡፡

Text Box: አንቀፅ 90 (3)፡- በህጉ ልዩ ክፍል ውስጥ የእስራት ቅጣት ብቻ በተደነገገ ጊዜና ተቀጭው የህግ ሰውነት ያለው ድርጅት በሆነ ጊዜ እስከ አምስት አመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር አስር ሺህ፣ እስከ አምስት አመት ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር 20 ሺህ፣ እስከ አስር አመት ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ እስከ ብር 50 ሺህ ከአስር አመት በላይ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን ከ100ሺህ እስከ 500 ሺህ በሚደርስ ቅጣት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡

  1. በዚህ አንቀፅ ከተቀመጠው ቅጣት በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛው ከመንግሥት ጋር ማናቸውንም ዓይነት ውል ወይም ግብይት በዘላቂነት ወይም ለተወሰነ ጊዜ እንዳይፈፀም የሚከለክል ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

አንቀፅ 428 ዋጋ ያለውን ነገር ያለክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ መስጠት

ማንኛውም ሰው በአንቀፅ 417 በተመለከቱት ሁኔታዎች ለማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ከእርሱ ጋር ግንኙነት ላለው ማንኛውም ሌላ ሰው ያለክፍያ ወይም ያለበቂ ክፍያ ማናቸውንም ዋጋ ያለው ነገር ያቀረበ፣ የሰጠ፣ ወይም ለመስጠት የተስማማ እንደሆነ፣ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 429 ማቀባበል

ማንኛውም ሰው ለራሱ ማናቸውንም አይነት ጥቅም ባያገኝም እንኳ የመንግሥት ስራን ለሚያከናውን ሰው ጉቦ ለመስጠት ገንዘብ፣ ዋጋ ያለው ነገር፣ አገልግሎት ወይም
ሌላ አይነት ጥቅም ከሌላ ሰው የተቀበለ እንደሆነ፣ ወይም የራሱን የባንክ ሂሳብ እንደዚህ አይነት ጉቦ ለማቀባበል ያዋለ እንደሆነ፣ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 43ዐ በሌለው ስልጣን መጠቀም

    ማንም ሰው፡-

ሀ. ከመንግሥት ስራው ከታገደ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ፣ ከተወገደ ወይም ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከተወ በኋላ በስራው ላይ ያለ በማስመሰል፣

      ለ. ለወደፊቱ የመንግሥት ሠራተኛ እሆናለሁ ብሎ በማመን ወይም፣

ሐ. የመንግሥት ሠራተኛ ሳይሆን መስሎ በመቅረብ፣ ይህንን አደርጋለሁ በማለት የተስፋ ቃል በመግባት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ወይም ስጦታ ከሌላ ሰው ላይ የጠየቀ ወይም የተቀበለ እንደሆነ፣ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እሥራት፣ ወይም ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 431 በግል ተሰሚነት መነገድ

ማንም ሰው የመንግሥት ሠራተኛ ባለመሆኑ ለመንግሥት ሠራተኛ የተደነገገው /የወንጀል ህጉ አንቀፅ 414/ የማይመለከተው ቢሆንም፣ ያለውን ወይም እንዳለው ያስመሰለውን ተሰሚነት በመጠቀም በአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ልዩ መብት ወይም ጥቅም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ሲል ከሌላው ሰው ገንዘብ፣ ስጦታ፣ እጅ መንሻ ወይም ሌላ ጥቅም የጠየቀ፣ የተቀበለ ወይም እነዚህን በተመለከተ የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ፣ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እሥራት ወይም ከሁለት ሺህ ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል፡፡

አንቀፅ 468 በምርጫ ላይ የሚሰጥ መደለያ

  1. ማንም ሰው የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት ያለውን ሌላውን ሰው በመብቱ በተወሰነ መንገድ እንዲጠቀም ወይም መብቱን እንዲተው ለማድረግ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ገንዘብ፣ ወይም ማናቸውንም ሌላ ዓይነት ጥቅም የሰጠ፣ ወይም ለመስጠት ቃል የገባ እንደሆነ፣ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡
  2. የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት ያለው ማንም ሰው በዚሁ መብቱ እንዲጠቀምበት፣ ወይም በአንድ በተወሰነ መንገድ እንዲጠቀምበት ወይም ሳይጠቀምበት እንዲቀር ገንዘብ ወይም ማናቸውንም ሌላ ዓይነት ጥቅም የተቀበለ ወይም ለመቀበል የተስማማ እንደሆነ፣ ከዚህ በላይ በተመለከተው ቅጣት ይቀጣል፡፡

 አንቀፅ 676 ከባድ የእምነት ማጉደል

  1. ወንጀሉ የተፈፀመው፣ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ንብረት ላይ ከሆነ ወይም ወንጀሉን የፈፀመው የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ሹም ወይም የሕዝብ ባለአደራ ወይም ተመራጭ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከብር አንድ መቶ ሺህ የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
  2. ወንጀሉ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣው፡-

ሀ. ወንጀሉን የፈፀመው ሞግዚት ወይም ንብረት ጠባቂ፣ ሂሳብ አጣሪ፣ የሕግ ወይም የገንዘብ አማካሪ፣ ወኪል፣ ጠበቃ፣ የንብረት አስተዳዳሪ ወይም በሥራው ወይም በተሰጠው ኃላፊነት ምክንያት ንብረቱ በእጁ የገባ ማንኛውም ሌላ ሰው እንደሆነ፣ ወይም

ለ. ተከሳሹ በእምነት በተቀበለው ሰነድ ላይ ሰጪውን ባለዕዳ የሚያደርግ ግዴታ አስመስሎ በመፃፍ ወይም የገንዘብ መቀበያ ሰነድ በማስመሰል ወይም በፈራሚው ንብረት ላይ ጉዳት በሚያደርስ በማናቸውም ሌላ አይነት አድራጐት ሠርቶበት እንደሆነ ወይም

ሐ. ወንጀሉን የፈፀመው ስለገንዘብ መሰብሰብ ለሕዝብ ጥሪ የሚያደርግ ሰው ሆኖ ለራሱ ወይም ለአንድ የንግድ ማህበር ወይም ለባንክ ወይም ለሌላ ድርጅት ጥቅም ሲል ገንዘብ ወይም ዋጋ ያላቸውን ነገሮች የሚሰበስብ ሰው እንደሆነ ነው፡፡

አንቀፅ 684 በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና በወንጀሉ መርዳት

  1. ማንም ሰው በሙስና፣ በአደንዛዥ ዕጽ ወይም መድሃኒት ዝውውር፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ ወይም በወንጀል ሕጉ፣ በአንቀፅ 233(2)(3)፣ 262(1)(2)፣ 425(2)፣ 5ዐ6(3)(4)፣ 507 እስከ 5ዐ9፣ 51ዐ(2)፣ 511(2)(3)(5) ወይም 512 በተመለከተው ወንጀል ወይም በማናቸውም ተመሣሣይ ከባድ ወንጀል አማካኝነት ያገኘውን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕገወጥ  አመጣጥ ሰውሮ በጥቅም ወይም በስራ ላይ በማዋል፣ በማዘዋወር ወይም በማስተላለፍ ሕጋዊ አስመስሎ ያቀረበ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራትና ከመቶ ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  2. ማንም ሰው በንዑስ አንቀፅ (1) ከተመለከቱት የወንጀል ድርጊቶች በአንዱ የተገኘ መሆኑን እያወቀ ሕገወጥ የሆነን ገንዘብ ወይም ንብረት፣ የለወጠ፣ ያስተላለፈ፣ የተቀበለ፣ ይዞ የተገኘ ወይም በዚሁ ገንዘብ ወይም ንብረት የተጠቀመበት እንደሆነ፣ ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) በተመለከተው ቅጣት ይቀጣል፡፡
  3. ማንም ሰው ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) ወይም (2) የተገለፀው ወንጀል መፈፀሙን እያወቀ ወይም ለማወቅ የሚያስችለው በቂ ምክንያት እያለው አግባብ ላለው ባለስልጣን ሳያሳውቅ የቀረ እንደሆነ ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
  4. ማንም ሰው ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) እና (2) የተገለፀውን ወንጀል በተመለከተ ፖሊስ ክትትል እያደረገ ወይም በቅርቡ ሊያደርግ መሆኑን፣ ጥቆማ መቅረቡን፣ ወይም በውስጥ ደንብ መሠረት ጉዳዩ ለሚመለከተው ሠራተኛ የተላለፈ መሆኑን አውቆ ወይም ጠርጥሮ በወንጀሉ ለተጠረጠረው ወይም ለሌላ ሰው መረጃ የሰጠ ወይም ወሬ ያቀበለ እንደሆነ፣ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡
  5. ማንም ሰው ከላይ በንዑስ አንቀፅ (1) በተገለፀው ወንጀል የተገኘ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወንጀሉን የሚፈፅመውን ሰው ለመርዳት ወይም ንብረቱ የተገኘበትን ሕገወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሰወር በማሰብ ንብረቱ ሕጋዊ እንዲሆን ያደረገ ወይም ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ያዘዋወረ እንደሆነ ወይም እውነተኛ ባህሪውን፣ ምንጩን፣ የሚገኝበትን ቦታ፣ ግብይቱን፣ እንቅስቃሴውን ወይም ከንብረቱ የሚመነጭ መብትን እንዳይታወቅ ያደረገ ወይም የሠወረ እንደሆነ ከላይ በንዑስ አንቀፅ 1 የተመለከተውን ቅጣት ይቀጣል፡፡
  6. የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት ከላይ ከተመለከቱት ወንጀሎች በአንዱ ተካፋይ ሲሆን ቅጣቱ የሚወሰንበት በወንጀል ህጉ በአንቀፅ 9ዐ በተደነገገው መሠረት ነው፡፡
  7. በዚህ አንቀፅ መሠረት ከባድ ወንጀል ማለት፡-

ሀ. ወንጀሉ አስር ዓመት ጽኑ እሥራት ወይም ከዚያ በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ሲሆን፣ ወይም

ለ. በወንጀሉ አማካይነት የተገኘው የገንዘቡ መጠን ወይም የንብረቱ ዋጋ ቢያንስ ሃምሳ ሺህ ብር ሲሆን ነው፡፡

አንቀፅ 696 ከባድ አታላይነት

ከባድ የአታላይነት ወንጀል ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራትና እስከ ብር ሃምሣ ሺህ በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣው፡-

ሀ. ጥፋተኛው በአንቀፅ 676(1) እና (2) (ሀ) በተገለፀው መሠረት እምነት በሚጣልበት የሥራ ደረጃ ወይም ኃላፊነት ላይ የሚገኝ እንደሆነ፣ ወይም

ለ. አድራጊው የማህበር፣ የባንክ፣ የንግድ፣ የአክሲዮን ገበያ ወይም የኢንዱስትሪ መሥሪያ ቤት አክሲዮን፣ የዕዳ ሰነድ፣ የቦንድ ወይም ማናቸውንም የዋስትና ሰነድ በማውጣት ከሕዝብ ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥሪ ያደረገ ወይም ለራሱ ወይም ለድርጅቱ ወይም አድራጊው የአክሲዮን ባለድርሻ ለሆነበት ድርጅት የሸጠ እንደሆነ ወይም፣

        ሐ. ወንጀሉ የተፈፀመው በሕዝብ አስተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ  እንደሆነ ነው፡፡

   13 አህጉራዊና አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ስምምነቶችን በተመለከተ

ሙስና የአንድ አካባቢ ወይም የአንድ አገር ችግር ተደርጎ የሚቆጠርበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን አሁን ሙስና የብዙ አገራትን ህዝቦች እያሰቃየ ያለ ድምበር ተሻጋሪ ችግር ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህም ሙስና በትብብር የሚዋጉት እንጅ በተናጠልና ዘለቄታዊነት በሌለው  መንገድ ሊያሸንፉት የሚሞክሩት ጠላትም አይደለም፡፡ ይህን ትብብር ለማጠናከር አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንካራ የፀረ-ሙስና ስምምነቶችን መፈራረምና እነዚህን ስምምነቶች በትብብር መተግበር ይጠበቅበታል፡፡

 

አገራችን  ለፈረመቻቸው የእዚህ አይነት ስምምነቶች ተገዥ ከመሆኗም በላይ ለአፈፃፀማቸውም ከተለያዩ አገራትና ድርጅቶች ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ ናት፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽኖች አጽዳቂ አገር መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ በርግጥ አገራችን በእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ ያሉ መርሆዎችንና ድንጋጌዎችን ስምምነቶቹን ከማፅደቋ በፊትም ቢሆን እየተገበረች የቆየች ቢሆንም ከስምምነቶቹ በኋላ ደግሞ በስምምነቱ የተቀመጡ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግሉን የምታጠናክር ይሆናል፡፡

   14 ኮሚሽኑ ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሙስና ተቋማት ልምዶችን ለመቅሰም ያደረጋቸው ጥረቶች

በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመግለጽ እንደተሞከረው ከኮሚሽኑ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የአቅም ውስንነት አንዱ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች በመንደፍ የአቅም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይም ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴዎች ልምድ በመቅሰም ይህንን ተሞክሮ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በመተግበር አንፃር ኮሚሽኑ አበረታች ሥራ ሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ከተጠቀሰው ልምድ መጋራት አኳያ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን መዘርዘር የተደረገውን ጥረት ለማሳየት ይረዳል ብለን እናምናለን፡፡

ኮሚሽኑ ከሆንግኮንግ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር የፈጠረው የስራ ግንኙነት እና በዚህም አማካኝነት ያገኘው ተሞክሮ ተጠቃሽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 አምስት አባላት ያሉት የኮሚሽኑ የልዑካን ቡድን በሆንግኮንግ የ11 ቀናት ጉብኝት በማድረግ ከአቻው የፀረ-ሙስና ተቋም ጠቃሚ ልምዶችን ወስዷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 15 አባላት ያሉት የኮሚሽኑ ልኡካን ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሆንግ ኮንግ በመሄድ ተመሳሳይ ልምዶችን አግኝቶ ተመልሷል፡፡ እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ሌላው ጉዳይ የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ሲቋቋም እንደዋነኛ ሞዴል የወሰደው የሆንግ ኮንግ የፀረ-ሙስና ተቋምን አሠራር እና አደረጃጀት እንዲሁም አቅጣጫ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኮሚሽኑ ልኡካን ቡድኖች ወደ ሲንጋፖር፣ ቻይናና ማሌዥያ ተጉዘው ሙስናን በመከላከልና በመዋጋት ረገድ ልምድ ቀስመው የተመለሱበት አጋጣሚ ነበር፡፡

የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች የነበረውን ተሳትፎ በተመለከተ በበርካታ ኮንፈረንሶች ተገኝቶ ኢትዮጵያ ሙስናን በመታገልና በመከላከል ረገድ እያደረገች ያለውን ጥረት ለሌሎች ለማሳወቅ ጥረት ከማድረጉም በተጨማሪ ከመድረኮቹ የተለያዩ ልምዶች ወስዷል፡፡ በዚህ ረገድ በቪየና (ኦስትሪያ) እና እ.ኤ.አ 2ዐዐ6 በሜሪዳ (ሜክሲኮ) እ.ኤ.አ 2ዐዐ3 የተባበሩት መንግስታትን የፀረ-ሙስና ስምምነቶች ለማርቀቅ እና ለፊርማ ለማዘጋጀት በተደረጉት ኮንፈረንሶች ላይ ኮሚሽኑ ተገኝቶ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እንዲሁም በፕራግ (ቼክ ሪፐብሊክ) በተካሄደው አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ኮንፈረንስ ላይ ኮሚሽኑ ተሳትፏል፡፡ ኮሚሽኑ በዋሽንግተን ዲሲ እ.ኤ.አ (የካቲት 17-19 ቀን 1991 ዓ.ም)፣ ዘሔግ (ሆላንድ) (ከግንቦት 20-23 ቀን 1993 ዓ.ም)፣ ሴኡል (በደቡብ ኮሪያ) (ከግንቦት 29-31ቀን 1995 ዓ.ም) እንዲሁም ብራዚሊያ (በብራዚል) (ከግንቦት 30-ሰኔ 3 ቀን 1997 ዓ.ም) በተካሔዱት አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና መድረኮች ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ባንኮክ (ታይላንድ) እ.ኤ.አ ከሚያዚያ 17-20/2007 በተካሔደውና በአለም አቀፍ የፋይናንስ ወንጀሎች ዙሪያ ባተኮረው አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ኮሚሽኑ ያደረገው ተሳትፎም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ሙስናን ዘርፍ ተኮር በሆነ መንገድ ለመታገል ከተደራጁ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያደርግ የነበረው የስራ ትብብርም በበጐ ጐኑ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለምሳሌ በግንባታው ዘርፍ ሙስናን ለመታገል በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቋቋመው Construction Sector Transparency Initiative (CoST) ጋር ኮሚሽኑ በትብብር ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት ይህ ኢኒሸቲቭ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ለንደን (እንግሊዝ) ሔልሲንኪ፣ (ፊንላንድ) አዲስ አበባ፣ ወዘተ) ባካሔዳቸው ጉባኤዎችም ኮሚሽኑ ተሳታፊ ነበር፡፡ በአገራችን የግንባታ ዘርፍ በፍጥነት እያደገ በሚገኝበት እና ሰፊ ምዕዋለ ንዋይ በሚመደብለት ሁኔታ ውስጥ መገኘታችን ይህን መሰሉ ኢንሼቲቭ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እውን ነው፡፡ ኮሚሽኑ በማዕድን ሐብቶች አጠቃቀም የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል ከተቋቋመው Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) ከተባለ አለም አቀፍ ድርጅት ጋርም አብሮ ለመስራት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 በሉሳካ (ዛምቢያ) በተካሄደው የፓን አፍሪካን የፀረ-ሙስና ኮንፈረንስ ላይም ኮሚሽኑ ተሳትፏል፡፡ በተጨማሪም በቅደም ተከተል በቤይጅንግ (ቻይና)፣ ባሊ (ኢንዶኔዢያ) እንዲሁም ኪየቭ (ዩክሬን) በተካሔዱት በ1ኛው፣ 2ኛውና 3ኛው የአለም አቀፍ የፀረ-ሙስና አካላት ኮንፈረንሶች ላይም ኮሚሽኑ ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ በዋርሶ (ፖላንድ) እ.ኤ.አ 2ዐዐ6 በፀረ-ሙስና እንቅስቃሴዎችና በሰባዊ መብቶች ጥበቃ ዙሪያ በተካሔደው አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይም ተገኝቶ የበኩሉን አስተዋፆ አበርክቷል፡፡

በፀረ-ሙስና ትግሉ ዙሪያ የተደረጉ ምክክሮችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ከአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ ከአለም ባንክ፣ ከመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP)፣ ከቻይና የህግ ባለሙያዎች ማህበር፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል፣ ከእንግሊዝ የኦዲት ቢሮ፣ እና ከሌሎችም ጋር የተደረጉ ውይይቶች ለአገራችን የፀረ-ሙስና ትግል ጠቃሚ ነበሩ፡፡

በተጠቀሱት መድረኮች እና ግንኙነቶች አገራችን ያደረገችው ተሳትፎ ሙስናን በመታገልና በመከላከል ረገድ ከሌላው አለም ጋር አብሮ ለመስራት ያላትን ፅኑ ፍላጎት ያሳያል፡፡ በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን ዲሴምበር 9 ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በተከታታይ ዓመታት በድምቀት ስታከብር መቆየቷም በፀረ-ሙስና ትግሉ ሊኖር በሚገባው አለም አቀፍ ትብብር ላይ ያላትን ጠንካራ አቋምና እምነት የሚያሳይ ነው፡፡

   15 ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች

    ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ አመታት ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት ባደረገው ጥረት የተለያዩ ችግሮች ገጥመውታል፡፡ ከአቅም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ በዋና ዋና የስራ ሒደቶች ማለትም በስነምግባር ትምህርት፣ በሙስና ወንጀሎች ምርመራና ክስ እንዲሁም በሙስና ወንጀል መከላከል ረገድ የተሠማራው ባለሙያ በሚፈለገው ደረጃ አቅሙ የተገነባ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በሁሉም የሥራ ዘርፎች በተለይ ሙስናን ከመታገል አንፃር የተሟላ ክህሎት አለ ማለት አያስደፍርም በዚህ ረገድ ባለሙያዎችን የሚያበቃና የተለየ ስልጠና የሚሰጥ ተቋም አለመኖሩ ለችግሩ አንዱና ዋነኛ ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ኮሚሽኑ ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ የቆየው፡፡

ሌላው ኮሚሽኑን ያጋጠመው ችግር ሙስናን በመከላከል እና በመዋጋት/በመታገል ረገድ የህብረተሰቡ ፍላጐት እጅግ የላቀ መሆኑ እና ኮሚሽኑ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ፍላጐት ለማሟላት አለመቻሉ ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ሙስና በጥቂት አመታት ውስጥ እንዲወገድ ይጠብቃሉ፡፡ የተወሰኑት ወገኖቻችን ደግሞ ምንም ተጨባጭ ማስረጃ በማይቀርብበት ሁኔታ የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት የፀረ-ሙስና ትግሉን የሚጎዳ አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የፀረ-ሙስና ትግሉ በአንድ ወይም በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ የሚሳካ አድርገው የሚቆጥሩ አሉ፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ እነዚህን የተዛቡ አመለካከቶች ለመቀየር ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ያምናል፡፡

አገራት (ኢትዮጵያን ጨምሮ) የሙስና ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ የሁለትዮሽ የጋራ ስምምነት (Extradition Treaty) በአብዛኛው ያልተፈራረሙበት ሁኔታ መኖሩም እንደ ችግር የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ብዙ ሙሰኞች ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ እንዲያመልጡ የሚያደርግበት አጋጣሚ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ይህ ሁኔታ በአገራችን የፀረ-ሙስና ትግል ውስጥ የተወሰነ ጫና ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሙሰኞች የህዝብ ሐብት ዘርፈው በአንዳንድ የምዕራብ አገራት ጥገኝነት በመጠየቅ ለሰሩት ወንጀል ሳይጠየቁ ያለችግር የሚኖሩበት ሁኔታ አለ ፡፡ ይሁንና ከላይ በጠቀስነው ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት አለመኖር ምክንያት እነዚህን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ለፍርድ ለማቅረብ የማይቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ አገራችን በተለያየ አጋጣሚ የተወሰኑ ሙሰኞችን ከውጭ አገር እንዲመለሱ ያደረገችበት ሁኔታ የነበረ ቢሆንም ይህን ተግባር በተፈለገው መልኩ እያከናወነች ባለመሆኗ ችግሩን መጋራት አልቀረም፡፡

በዚህ ረገድ የመንግስታቱ ድርጅት የአደንዛዥ እፅና የወንጀል መከላከል ቢሮ (UNODC) እና የአለም ባንክ በትብብር StAR Initiative በሚል ስያሜ ያቋቋሙት ድርጅት ወደፊት የዚህ አይነት ችግሮችን ለመፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባንኪ ሙን በአንድ ወቅት እንዳሉት ኢኒሸቲቩ በሙስና የተዘረፉ ሐብቶችንና ንብረቶችን ወደ ህጋዊ ባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ በማስቻል ረገድ ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገራት እንዲሁም በግልና መንግስታዊ በሆኑ ድርጅቶች መካከል የሚደረገውን ትብብር ማሳደግ የፀረ-ሙስና ትግሉን ያጠናክራል፡፡

ስታር ኢኒሼቲቭ በዋነኝነት የተቋቋመው በቀድሞ መሪዎቻቸው ሐብትና ንብረታቸው የተዘረፈባቸው ታዳጊ አገራት ሐብታቸውን በማስመለስ ለልማት እንዲጠቀሙበት ለማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም ኢኒሼቲቩ የታዳጊ አገራት መሪዎች የህዝብ ሀብት ነጥቀው በምዕራብ አገራት የሚሸሸጉበትን ሁኔታ ለማጥበብ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል፡፡

በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ችግር በተለያዩ የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴዎች የአገራት ትብብር ማነስ ነው፡፡ ለምሳሌ በአቅም ግንባታ፣ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ፣ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ስምምነቶች አፈፃፀም፣ ወዘተ በአለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ትብብሮች አሉ ለማለት አያስደፍሩም፡፡ ይህም በመሆኑ አገራችን ከዚህ መሰሉ ትብብር የምታገኘውን ጥቅም ማጣቷ አይቀርም፡፡

ሌላው የሚጠቀሰው ችግር የፍትህ አካላት የሙስናን ልዩና ውስብስብ ባሕሪያት እንዲሁም የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በሚፈለገው ደረጃ ተገንዝበው ወንጀሉን ለመከላከልም ሆነ ለመዋጋት በሚያስችል መልኩ አለመንቀሳቀሳቸው እንደችግር የሚነሳ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ችግር በወሳኝ መልኩ ለማስወገድ በተለያዩ መድረኮች በሚደረጉ ግንኙነቶች እና በግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች አማካኝነት ለማስወገድ ሳያሰልስ እየሠራ ይገኛል፡፡

የፀረ-ሙስና ትግሉን ጠቀሜታ በውል ባለመረዳት፣ አንዳንዴም ከፍላጐት ማነስ የአንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኃላፊዎች ደግሞ በየመስሪያ ቤቶቻቸው ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት በሚፈለገው መጠን አለማጠናከራቸው ሌላው ኮሚሽኑ እንደችግር የሚያነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ እነዚህ ኃላፊዎች ተገቢው ሚናቸውን እንዲጫወቱ ለማድረግ ኮሚሽኑ በተለያይ መንገዶች ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በሂደትም የተሻለ ሁኔታ እንደሚፈጠርም እምነቱ ነው፡፡

ቀደም ብለው የተጠቀሱ ችግሮችን ለመቅረፍም ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራትና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት፣ የልምድ ልውውጦችን በማካሔድ፣ ወዘተ ለመፍታት ኮሚሽኑ ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የኮሚሽኑ ጥረቶች ብቻ ችግሮቹን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት አያስችሉም፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሮቹን በማቃለል እና በመፍታት ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብሎ ያምናል፡፡

  16 በተደጋጋሚ ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

@     ኮሚሽኑ ሙስናን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ ከፖለቲካ ተፅኖ ምን ያህል ነፃ ነው?

መልስ፡-በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 4 መሰረት ኮሚሽኑ በሚመረምራቸው ወይም ክስ በሚመሰርትባቸው ወይም ክስ በመሰረተባቸው ጉዳዮች ላይ ከማንኛውም ሰው ወይም አካል ጣልቃ ገብነትና አመራር ነፃ ነው፡፡ በተግባርም እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡

@     የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ኮሚሽኑ በስራ አስፈፃሚው ሊፈፀሙ የሚችሉ የሙስና ወንጀሎችን ለመመርመርና ለመክሰስ በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት አይፈጥርበትም?

መልስ፡-እስካሁን የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ በስራ አስፈፃሚው ውስጥ የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን ለመመርመርና አጥፊዎቹንም ለፍርድ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት ላይ እክል አልፈጠረበትም፤ ከዚህ ተግባሩም አላገደውም፡፡ እስካሁን የአንድም የሙስና ወንጀል ምርመራ ወይም ክስ በዚህ ምክንያት አልተቋረጠም፡፡ ተጠሪነትን በተመለከተ እንዲያውም አንዳንዶቹ የተቃራኒውን ጎራ ይዘው የሚከራከሩ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ሙስና (በተለይ በታዳጊ አገሮች) በዋናነት የሚፈፀመው በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ነው፡፡

እነዚህን ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውንም ከሌሎች ወገኖች በተሻለ የሚያውቃቸው ስራ አስፈፃሚው ራሱ ነው፡፡ ሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን እና የልማት ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የመከታተል እና የመቆጣጠር ህጋዊ ድጋፍ ስላለው በዚህ አካባቢ የሚፈፀሙ የሙስና ድርጊቶችን እና የሥነምግባር መጣሶችን በተሻለ ለመዋጋት ይችላል፡፡ በመሆኑም የእነዚህን ተቋማት ተጠሪነት ለስራ አስፈፃሚው ማድረግ ስራቸውን በትብብር ውጤታማ በሆነ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው እንጅ ለችግር የሚዳርጋቸው አይደለም ይላሉ፣ እነዚህ ወገኖች፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተግባር እንደሚታየው በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ጠንካራ የፀረ-ሙስና ተቋማትም መካከል ተጠቃሽ የሚሆኑት ሳይቀሩ ተጠሪነታቸው ለየስራ አስፈፃሚው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ረገድ በፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማ የሆኑ የሆንግ ኮንግ፣ የሲንጋፖር፣ እና የቦትስዋና የፀረ-ሙስና ተቋማት ተጠሪነት ለየስራ አስፈፃሚዎቻቸው ቁንጮዎች ነው፡፡ የአውስትራሊያ ግዛት የሆነችው ኒው ሳውዝዌልስ የፀረ-ሙስና ተቋም ተጠሪነትም እንዲሁ ለሥራ አስፈፃሚው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  

@     የኢፌዴሪ መንግስት ሙስናን በቁርጠኝነት ለመዋጋት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ልታስረዱኝ ትችላላችሁ?

 

መልስ፡- ያለ ሌላ ወገን ቀስቃሽነት ራሱን ፈትሾ ሙስና የሀገሪቷ ችግር መሆኑን ተቀብሎና ችግሩን ለመፍታት ወስኖ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር የሚከተሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

F     ማንም ሳይቀሰቅሰው ራሱን ፈትሾ ሙስና የሀገሪቷ ችግር መሆኑን ተቀብሎና ችግሩንም መፍታት አንዳለበት መወሰኑ፣

F     በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት ሙስናን በብቃት ለመታገል የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችን አውጥቶ ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ በወንጀል ህጉ ላይ በ23 አንቀፆች ተካተው የተቀመጡት የሙስና ወንጀል ህጎች፣ የተሻሻለው የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የሥነሥርአትና ማስረጃ ህግ፣ የተመራጮች፣ የተሸóሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች የሐብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 657/2ዐዐ2 የጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የተለያዩ ደንቦች ማውጣት እና ተግባራዊ መሆን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

F     የፀረ-ሙስና ትግሉን እንደ አንድ ብሔራዊ አጀንዳ በመያዝ በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ገለልተኛ የፀረ-ሙስና ተቋማትን አቋቁሞ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እየታገለው ይገኛል፡፡

F     የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ለፀረ-ሙስና ተቋማት ተገቢውን በጀት እና የሰው ኃይል የመመደብ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

F     የተሻሻለው የአገሪቱ የወንጀል ህግ የፀረ-ሙስና ህጎችን በ23 አንቀፆች አካቶ እንዲይዝ አድርጓል፡፡

F     አገራችን የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት የፀረ-ሙስና ስምምነቶችን ቀድመው ከፈረሙና ካፀደቁ አገራት መካከል እንድትሆን አድርጓል፡፡

F     የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ወይም ምክትል ኮሚሽነሩ አግባብነት ባለው የስነምግባር ደንብ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተላልፈው ካልተገኙ፣ ጉልሕ የሆነ የስራ ችሎታና ቅልጥፍና ችግር ካልታየባቸው በህመም ምክንያት ተግባራቸውን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር የስራ ዘመናቸው ከማለቁ በፊት ከፈቃዳቸው ውጭ ከስራቸው የማይነሱበትን ሁኔታ በአዋጅ አረጋግጧል፡፡

F     የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችም ሆነ የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት በሙስና ተዘፍቀው በተገኙ ጊዜ ያለማወላወል ተገቢ ቅጣታቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ማንም ከህግ በላይ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

F     በአጠቃላይ ከእስካሁኑ እንቅስቃሴዎቹ የሙስና ችግሮችንና ብልሹ አሰራሮችን በተመለከተ በንቃትና በቁርጠኝነት አምርሮ የሚጠላና የሚታገል መሆኑን አሳይቷል፡፡

@     በሙስና ተዘፍቀው የተገኙ የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲቀጡ አድርጓል ለተባለው ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል?

መልስ- የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቀድሞውን መከላከያ ሚኒስትር፣ ከፍተኛ የባንክና የቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት፣ የቀድሞው የፕራቬታይዜሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

@     ኮሚሽኑ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎችን የመመርመርና አጥፊዎቹንም የመክሰስ ስልጣን አለው?

መልስ፡-በዋነኝነት የኮሚሽኑ የስልጣን ክልል በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሙስናን በመከላከል፣ በመመርመርና በመክሰስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው ድጎማ ጋር በተያያዘ ሙስና ተፈፅሞ የተገኘ እንደሆነ ኮሚሽኑ ይህን የሙስና ወንጀል የመመርመርና በአጥፊዎቹ ላይ ክስ የመመስረት ስልጣን አለው፡፡ የግሉ ዘርፍ ከመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ጋር በሚያካሒዳቸው ተግባራት ውስጥ ሙስና ከተፈፀመም ኮሚሽኑ ይህን የሙስና ወንጀል የመመርመርና ክስ የመመስረት ስልጣን አለው፡፡

@     የኮሚሽኑን የስልጣን ክልል በዚህ መንገድ ለመወሰንና ለመገደብ ለምን አስፈለገ?

መልስ፡-ለጊዜውም ቢሆን የኮሚሽኑን የስልጣን ክልል በተጠቀሰው መንገድ ለመወሰን ያስፈለገበት በዋነኝነት በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ነው፡፡

F     በመጀመሪያ ደረጃ ከተቋቋመ ጥቂት አመታትን ያስቆጠረው ኮሚሽኑ በተጠቀሱት ጥቂት አመታት ውስጥ ባካበተው መጠነኛ ልምድና አሁን ባለው ሁለንተናዊ አቅም የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሙስናን የመመርመር፣ የመክሰስና የመከላከል ተግባራትን ያለችግር ለማከናወን ይቸገራል የሚል እምነት አለ፡፡ ኮሚሽኑ ውስን በሆነው አቅሙ ኃላፊነቱን በብቃት ይወጣ ዘንድ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ ከስትራተጂ አንፃርም የሚመረጥ ነው፡፡

F     በሁለተኛ ደረጃ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሙስና የመፈፀም እድሉ የሰፋ እንደሆነ ይታመናል፡፡ አብዛኛዎቹ የሙስና ወንጀሎችም በነዚህ መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኮሚሽኑን የስልጣን ክልል ከዚህ አንፃር ወስኖ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አሁን አሁን የኮሚሽኑ አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እያለ በመምጣቱ በተወሰኑ የግል ዘርፎች ሙስናን የመከላከሉን እና የመዋጋቱን ኃላፊነትም እንዲይዝ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው፡፡ ይህን ለማድረግም ጥናት እየተካሔደ ይገኛል፡፡

F     አገሪቱ ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን እና አወቃቀርን ስለምትከተል የክልል መንግሥታት የእራሳቸው ስልጣን ስላላቸው ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ በፌደራል ደረጃ ሊወሰን የቻለበት ሁኔታ አለ፡፡

@     ኮሚሽኑ የስልጣን ክልል ስር የማይወድቁት ወንጀሎች እጣ ፋንታ ምንድን ነው? እንዲሁ ይተዋሉ ወይስ በሌላ መንገድ የሚስተናገዱበት ሁኔታ አለ?

መልስ፡-በኮሚሽኑ የስልጣን ክልል ውስጥ የማይወድቁና ወደኮሚሽኑ የመጡ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች የሚጣሉበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም፡፡ የዚህ አይነት የሙስና ወንጀሎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ወደሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ይላካሉ፡፡ የሙስና ወንጀል ውጭ ያሉ ሌሎች ወንጀሎች ቢሆኑም ወደሚመለከታቸው ሌሎች አካሎች የሚላኩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ባለቤት ስላላቸው ሊጣሉ አይችሉም፡፡

@     የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎች ጥቆማዎቻቸውን ለኮሚሽኑ እንዴት ሊያቀርቡ ይችላሉ?

መልስ- የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎች ጥቆማዎቻቸውን ለኮሚሽኑ በሚከተሉት መንገዶች ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡

F     በኮሚሽኑ ነፃ የጥቆማ መስጫ ስልክ ቁጥር…..988

F     በአካል ለገሐር በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ቢሮ ቁጥር 214 በመምጣት

F     በፋክስ ቁጥሮች 251-115-536991 ወይም 251-115-533861

F     በኢ-ሜይል feacinv@ethionet.et

F     ፖ.ሳ.ቁ 34798 ወይም 34799

F     በቀጥታ ስልክ መስመር 251-115-527781/74 ወይም በፒቢኤክስ ስልክ ቁጥር 251-115-529100 የውስጥ መስመር 232

@     ጥቆማ አቅራቢዎች ጥቆማዎችን ሲያቀርቡ ስማቸውን የመግለፅ ግዴታ አለባቸው?

መልስ፡- ጥቆማ አቅራቢዎች ከፈቃዳቸው ውጭ ስማቸውን እንዲገልፁ አይገደዱም፡፡ ሥማቸውን ሳይገልፁ ጥቆማዎችን መስጠት ይችላሉ፡፡ እነሱ ከፈለጉ ብቻ ስማቸውን መግለፅ ይችላሉ፡፡ ይህ መብታቸው በህግ ማዕቀፍ የተቀመጠ ነው፡፡ በተሻሻለው የፀረ-ሙስና ልዩ የስነስርአትና የማስረጃ ህግ መሰረት የሙስና ወንጀል ጥቆማን ስምን በመግለፅ ወይም ሳይገልፁ መስጠት ይቻላል፡፡

@     ጥቆማውን የሚቀርበው በቃል ነው ወይስ በጽሑፍ?

መልስ- ጠቋሚዎች ጥቆማዎቻቸውን በቃል ወይም በፅሑፍ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

@     አልፎ አልፎ ጥቆማዎች በአግባቡ ሳይመረመሩ እንደ አልባሌ ነገር ቆሻሻ መጣያ ውስጥ የሚጣሉበት ሁኔታ አለ የሚሉ ጥቂት ወገኖች አሉ፡፡ ይህ በእውነት የሚፈፀም ድርጊት ነውን?

 

መልስ፡- ኮሚሽኑ በስልጣን ክልሉ ውስጥ የሆኑና ከማንኛውም ወገን የሚቀርቡ ጥቆማዎችን የሚጥልበት ሁኔታ ፍፁም የለም፡፡ ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ያቀረቡ ወገኖች የጥቆማዎቻቸው ሁኔታ ምን ላይ እንደሚገኝ  የሚያረጋግጡበትንና መረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታና አሰራር ዘርግቷል፡፡ ይህን መብታቸውን ተጠቅመው ችግሮች ገጥመውናል ብለው የሚያስቡ ከሆነ ቅሬታቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህን ባደረጉ ጊዜ ኮሚሽኑ አፋጣኝ እርምጃዎችን ወስዶ ሁኔታዎችን የሚያስተካክልበት አሰራር ዘርግቷል፡፡

@     ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ ከግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም በፊት በምርመራና ክስ ላይ የነበሩ የሙስና ወንጀሎችን የመመርመር ስልጣን አለውን?

መልስ - በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀፅ 28 መሰረት ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ በፊት ተፈፅመው ምርመራቸው በሌሎች አካላት በጅምር ወይም በሂደት ላይ ያሉም ሆኑ የተጠናቀቁ ወይም በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያሉ የሙስናና ከሙስና ጋር የተያያዙ የወንጀል ጉዳዮች በነበሩበት ሁኔታ ቀጥለው ውሳኔ ያገኛሉ፡፡

@     የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች በመጠቆማቸውና በመመስከራቸው ምክንያት የብቀላ ሰለባ እንዳይሆኑ ዋስትና ሊሰጣቸው ይችላል?

መልስ-ኮሚሽኑ የሙስና ወንጀል ጠቋሚዎችና ምስክሮች የብቀላ ሰለባ እንዳይሆኑ ለመከላከል የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ የብቀላ እርምጃ የተወሰደባቸው ካጋጠሙም ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ይህንኑ ለማስተካከል አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ እስካሁን ባለው አሠራርም ቢሆን ኮሚሽኑ ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ ድጋፍ አለው፡፡ ይሁንና የጥበቃና የከለላ አድማሱን በማስፋት ረገድ የማርቀቅ ሥራው ተጠናቆ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የቀረበው የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መጽደቅ የራሱ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለ፡፡  

@     የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮና የክልል የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች የስልጣን ተዋረድ ምን ይመስላል? የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ሊቆጣጠራቸው ይችላል?

መልስ-የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ የክልል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖችን የመቆጣጠርና ይህን አድርጉ ያን አታድርጉ የማለት ስልጣን የለውም፡፡ የእነዚህ ተቋማት ተጠሪነት ህገመንግስታዊ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ላቋቋሟቸው የክልል መንግስታት እንጂ ለፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ አይደልም፡፡ የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮና የክልል አቻዎቹ ለአገራዊው የፀረ-ሙስና ትግል ተባብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በአቅም ግንባታና ልምድን በመለዋወጥ ረገድ የሚያሳዩት ትብብር አበረታች የሚባል ነው፡፡ የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ከነዚህ የክልል አቻዎቹ ጋር የጋራ የትብብር መድረክ አቋቁሟል፡፡ እስካሁን መድረኩ በአመት ሁለት ጊዜ በአጠቃላይ ስምንት ያህል የጋራ ጉባኤዎችን አካሒዷል፡፡

@     ይህ ማለት የክልል የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች በምንም መንገድ ለፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ተጠሪ የሚሆኑበት ሁኔታ የለም ማለት ነው?

መልስ-ፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና በመክሰስ ረገድ ከሚሰጣቸው ውክልናዎች ጋር በተያያዘ ለፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ተጠሪ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ እንዲሁም በአገር ደረጃ አንድ የተጠቃለለ መረጃ ይኖር ዘንድ በየክልሎቻቸው እየተካሔደ ስለሚገኘው የፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ ለፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ሪፖርት የሚያቀርቡበት ሁኔታም አለ፡፡

@     ሌሎች አካላት የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና በመክሰስ ረገድ የሚሳተፉበት ሁኔታና አሰራር አለ?

መልስ፡-የሙስና ወንጀል ምርመራን በተመለከተ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 8 ላይ እንደተመለከተው ከባድ ያልሆነ የሙስና ወንጀልን የመመርመር ጠቅላላ ውክልና ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል እንደሁኔታው ለፌደራል ወይም ለክልል የወንጀል መርማሪ አካላት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ክስ መመስረትን በተመለከተ ደግሞ በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 9 መሰረት ኮሚሽኑ ከአቃቤ ህግነት ስልጣኑ ውስጥ አግባብነት ላለው የፌደራል ወይም የክልል አቃቤ ህግ ወይም የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ተቋም በሙሉ ወይም በከፊል ውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም በተጠቀሰው መንገድ ውክልና ያልተሰጠው ማንኛውም ወንጀልን ለመመርመር ስልጣን ያለው የፌደራል ወይም የክልል መንግስታዊ አካል በኮሚሽኑ የስልጣን ክልል ስር የሚወድቅ የሙስና ወንጀል ለመፈፀሙ ጥቆማ ሲደርሰው ወይም በቂ ጥርጣሬ ሲኖረው ምርመራ መጀመር ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ስለተጀመረው ምርመራ ለኮሚሽኑ ሳይዘገይ ያሳውቃል፡፡

@     የሙስና ወንጀልን የማስታወቅና የመተባበር ግዴታ አለብኝ?

መልስ- የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ሰራተኞቻቸውና ኃላፊዎቻቸው የሙስና ወንጀል የተፈፀመ ስለመሆኑ ወይም ሊፈፀም በዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ሲደርሳቸው ወዲያውኑ ለኮሚሽኑ ወይም ስልጣን ላለው የምርመራ አካል የማስታወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ሰው ከኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር ጋር በተያያዘ ለሚጠየቀው ትብብርና ድጋፍ የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ የሙያ ድጋፍን በተመለከተ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

@     ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን የሚያቆይበት የራሱ የሆነ የማቆያ ቦታ በግቢው ውስጥ አለውን?

መልስ፡-እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ ተጠርጣሪዎችን የሚያቆይበት የራሱ የሆነ የማቆያ ቦታ የለውም፡፡ ተጠርጣሪዎችን በፖሊስ ጣቢያዎች የሚያቆይበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ወደ ፊት ግን የራሱን የማቆያ ጣቢያ ለማዘጋጀት ሐሳብ አለው፡፡

v      በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ግለሰብ በዋስ ሊለቀቅ ይችላልን?

መልስ፡-የተሻሻለው የኮሚሽኑ የፀረ-ሙስና ልዩ የስነስርአትና የማስረጃ ህግ አንቀፅ 4 እንደሚያብራራው በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም የተከሰሰበት ወንጀል ከአስር አመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መልቀቅ አይቻልም፡፡

  17 ማጠቃለያ

    

የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ ከተቋቋመ ከግንቦት 1993 ዓ.ም ጀምሮ ሙስናን በመዋጋትና በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ ስኬቶቹን በየዘርፉ ለመጥቀስ ያህል በሽዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የፊት ለፊት የስነምግባርና የፀረ-ሙስና ትምህርቶችን በመስጠትና የሙስናን አደገኝነት በተመለከተ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግሉን አገራዊ አጀንዳ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ሙስናን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ደግሞ ከ160 በላይ በሚሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ለሙስና የተጋለጡ ናቸው በሚባሉ የአሰራር ስርአቶች ላይ ጥናቶችን በማካሔድ ለሙስና በር የሚከፍቱ ቀዳዳዎችን ለመድፈን የሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን በእርምት እርምጃነት ለሚመለከታቸው ክፍሎች ለማቅረብ ተችሏል፡፡ የእነዚህን የማሻሻያ ሐሳቦችና እርምጃዎች አፈፃፀምም ከሞላ ጎደል ለመከታተል ተችሏል፡፡

በሙስና ወንጀል ክስና ምርመራ ረገድም ከ1,500 በላይ የሙስና ወንጀሎችን በመመርመርና በብዙዎቹ ላይ ክስ በመመስረት ከ520 በላይ የሚሆኑ ሙሰኞች ከ3-21 አመታት በሚደርስ የእስር ቅጣት (የገንዘብ ቅጣቱን ሳይጨምር) እንዲቀጡ ለማድረግ ተችሏል፡፡ እነዚህን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ሙሰኞች ከመስረቅና ከመዝረፋቸው በፊት ቆም ብለው ሁለቴ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ባጠቃላይ የተጠቀሱትን ውጤቶች ለማስመዝገብ ቢቻልም ሙስና የልማትና የዴሞክራሲያው ስርአት ግንባታ እንቅስቃሴዎቻችን እንቅፋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ግን ኮሚሽኑ ገና ብዙ መስራት እንዳለበት ያምናል፡፡

ኮሚሽኑ የተሻሉ ተግባራትን ያከናውን ዘንድ ደግሞ የባለድርሻና የመላ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ከእስካሁኑ በብዙ እጥፍ ማደግ አለበት፡፡ እነዚህ ወገኖች ከኮሚሽኑ ጋር በፀረ-ሙስና ትግሉ የሚያደርጉት ትብብር እጅግ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ወገኖች ተሳትፏቸውን ይጨምሩ ዘንድ ደግሞ የሙስናን ጎጅነት፣ መገለጫዎች፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ መንስኤዎች፣ ወዘተ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ የሚጨብጡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ይህን የተረዳው የፌ.ስ.ፀ.ሙ.ኮ በጠቀሱት ጉዳዮችና በሌሎችም ነጥቦች ዙሪያ የተለያዩ ወገኖች ግንዛቤ የሚጨብጡበትን ሁኔታ እያመቻቸ ይገኛል፡፡ ሁሉን አቀፍ መረጃ የያዘችው የዚች መጽሔት ዝግጅትም ከነዚህ ጥረቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ነው ይችን መጽሔት ለማዘጋጀትና ለመላ ህብረተሰቡ፣ ለባለድርሻ አካላትና ለአገሪቱ የልማት አጋሮች በሙሉ ለማሰራጨት ያስገደደን፡፡

በመጨረሻም የተያያዝነው የፀረ-ሙስና ትግል ይሰምር ዘንድ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና መላ ህብረተሰቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ ያላቸውን ተሳተፎ ከዚህ በበለጠ አጠናክረው በመቀጠል ሙስና የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን እንቅፋት እንዳይሆን እየተደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ትግል እንዲያጠናክሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

  18  ጠቃሚ አድራሻዎች

v      የክቡር ኮሚሽነር ጽ/ቤት

ስ.ቁ፡ 251-115-527784

ፋክስ፡ 251-115-527771

አ-ሜይል፡ feac.com@ethionet.et

v      የክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጽ/ቤት

ስ.ቁ፡ 251-115-527786

ፋክስ፡ 251-115-507801

ኢ-ሜይል፡ feacedum@ethionet.et

v      የስነምግባር ትምህርትና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-527785

ፋክስ፡ 251-115-536987

ኢ-ሜይል፡ feacedu@ethionet.et

v      የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-527787

ፋክስ፡ 251-115-536909

ኢ-ሜይል፡ feacprev@ethionet.et

v      የሙስና ወንጀሎች ምርመራና አቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-510554

ፋክስ፡ 251-115-533861

ኢ-ሜይል፡ feacpros1@ethionet.et

v      የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-536011

ፋክስ፡ 251-115-528980

ኢ-ሜይል፡ genzebs@yahoo.com

v      የስነምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-151506

ፋክስ፡ 251-115-151492

ኢ-ሜይል፡ ethicsco@ethionet.et

v      የእቅድ፣ ግዥና ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት

ስ.ቁ፡ 251-115-527783

ፋክስ፡ 251-111-556902

ኢ-ሜይል፡ feacplan@ethionet.et

v      የኮሚሽኑ ማዞሪያ፣ የፖ.ሳ.ቁና የድረ-ገጽ አድሻዎች

ስ.ቁ 251-115-529100

ፖ.ሳ.ቁ፡ 34798/9

ድረ-ገጽ፡ www.feac.gov.et