አገልግሎቱ ተጠሪነቱ ለፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆን በውስጡም ከአገልግሎቱ ኃላፊ በተጨማሪ የአንድ ኤክስፐርት፣ የአንድ ስታትስቲሽያን እና የአንድ ፀሐፊ የሥራ መደቦችን እንዲያካትት ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑም ሆነ የመምሪያዎችና የአገልግሎቶች የሥራ ዕቅዶች እና መርሐ ግብሮች እንዲሁም የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ዝግጅትን በማስተባበርና በማጠናቀር የተሟላ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያስችል ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ወቅታዊ የዕቅድ አፈፃፀም ክትትልና ግምገማ ያደርጋል፣ ለውሳኔ ያቀርባል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ የኮሚሽኑን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን ያዘጋጃል እቅዶችንም ለማስፈፀም በሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የገንዘብ እና የንብረት መጠን ላይ ጥናት በማድረግ ኮሚሽኑ ሊገጥመው የሚችለውን ችግር እንዴት መወጣት እንዳለበት መፍትሄ ይጠቁማል፡፡ 

አገልግሎቱ ከሚያከናውናቸው ሌሎች ዝርዝር ተግባራት መካከል፡- 

በዕቅድና ኘሮግራም አወጣጥና ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ላይ ኮሚሽነሩን፣ ም/ኮሚሽነሩንና ዳይሬክተሮችን ማገዝ እና ማማከር፣
የኮሚሽኑን የሥራ ዕቅዶችና ሪፖርቶችን ማጠናቀር፣ ማዘጋጀት፣ ለውሳኔ አመች በሆነ መልክ ለከሚሽነሩ ማቅረብና ማማከር፣
የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ እንደመረጃ ማዕከል ሆኖ ማገልገል፣
የኮሚሽኑን መሠረታዊ መረጃዎችን ማጠናቀርና ለመረጃነት ዝግጁ ማድረግ፣
በኘሮጀክቶች ዝግጅት ድጋፍ ማድረግና ኘሮጀክቶችን ማዘጋጀት፣
የኮሚሽኑ ስትራቴጅክ እቅድ እንዲዘጋጅ ማስተባበር/ የመሪነቱን ሚና መጫወት/ እና የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄድ ይገኙበታል፡፡